አልቃይዳ እና አይ ኤስ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት መግባታቸው ተገለጸ፡፡

445

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) ለዓመታት ጥምረት መሥርተው በማሸበር የሚታወቁት አልቃይዳ እና አይ ኤስ አይ ኤስ በሳኅል ቀጣና ጦር መማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡ በቅርቡ ሁለቱ ቡድኖች በመካከላቸው ስንጥቅ ተፈጥሮ እርስ በእርስ መታኮስ እንደጀመሩ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡

በመጀመሪያ በሶሪያ አካባቢ ይንቀሳቀሱ የነበሩት የሽብር ቡድኖቹ ወደ አፍሪካም ተስፋፍተው በሳኅል ቀጣና አካባቢ የተደራጀ ጥቃት ሲያደርሱ መቆየታውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

እ.አ.አ በ2012 በማሊ መንቀሳቀስ የጀመረው አልቃይዳ የሽብር ቡድን ይዞታውን እያስፋፋ በቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ጭምር ጥቃት ሲፈጽም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በሽዎች የሚቀጠሩ ወታደሮች ተገድለዋል፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተሰድደዋል፡፡

በቅርቡ ደግሞ በአሸባሪ ቡድኖቹ በመካከላቸው አልፎ አልፎ ይነሳ የነበረው ግጭት በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት መግቢያ አንስቶ እያደገ ሄዶ ወደ ለየለት ግጭት መግባታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ለአካባቢዎቹ ቅርበት ያላቸው የዘርፉ ልሂቃንና የአካባቢው መንግሥታት እንደገለጹት በማዕከላዊ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ አካባቢ አልቃይዳ እና አይ ኤስ አይ ኤስ ወደለየለት ጦርነት ገብተዋል፡፡ የግጭታቸው ምክንያት ደግሞ የግዛት ማስፋፋት እና ሰብል ማምረቻ ለም አካባቢዎች ላይ የተፈጠረ ይገባኛል መሆኑ ነው የተመላከተው፡፡

በተባሩት መንግሥታት ድርጅት የማሊ ልዩ ተወካይ ማሃማት ሳልህ አናዲፍ ‘‘የሁለቱ ነውጠኛ ቡድኖች ወደ ግጭት መግባት ድብቅ አይደለም፡፡ የማናውቀው የግጭታቸውን መቋጫ ነው፤ ሁለቱም የበላይነቱን መውሰድ ይፈልጋሉና፤ ለዚህም እየተፋለሙ ነው’’ ብለዋል፡፡

አልቃደይዳ በሰሜናዊ ማሊ እግሩን የተከለው በ2012 (እ.አ.አ) ነው፤ በኋላም ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር ኅብረት ፈጥሮ በማዕከላዊ ማሊ በ2015 (እ.አ.አ) የራሱን ይዞታ መሥርቷል፡፡

የአይ ኤስ የቀጣናው ታሪክ ግን ከአልቃይዳ አንጻር አጭር የሚባል ነው፡፡ እንደ ሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ አቡ ዋድ አል-ሳህሩይ ከተባለ ሰው ጋር በመጣመር ነው በ2015 አልቃይዳ የተመሠረተው፡፡ በዚህ ወቅትም በማሊ፣ ቡርኪናፋሶና ኒጀር ድንበር አካባቢ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበኢትዮጵያ ለኮሮና ቫይረስ መከላከልና ሕክምና ሊያግዙ የሚችሉ 58 የባህል መድኃቶች ለኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፍተሻ ተሰጡ፡፡
Next articleዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ለደንበኞቹ የወለድ ቅናሽ አደረገ፡፡