በ146 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተስፋፋ አደገኛ መጤ አረም ማስወገዱን የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

39

ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ከፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ከባለድርሻ አካላት እና በየደረጃው ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚቆይ ስልጠናዊ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ መጤ እና ወራሪ አረም በአካባቢ ሥነ ምኅዳር፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ሰፊ ችግር እያደረሰ ነው ብለዋል።

በተለይም እምቦጭ አረም እንደ ጣና ሐይቅ ያሉ የውኃማ አካላትን ሥነ ምኅዳር እያዛባ መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ እየተስፋፋ የመጣውን አደገኛ አረም በዘላቂነት ለማስወገድ የሚመለከታቸው ተቋማት በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ባለሙያ አወቀ ይታይ እንዳሉት በክልሉ 12 የሚኾኑ አደገኛ፣ መጤ እና ተስፋፊ አረሞች ተለይተዋል። 740 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በአደገኛ መጤ እና ወራሪ አረም ተሸፍኗል።

ባለሙያው እንዳሉት አረሙን በየጊዜው የማስወገድ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በ2017 ዓ.ም ለማስወገድ በዕቅድ ከተያዘው 180 ሺህ ሄክታር መሬት በዘጠኝ ወሩ 146 ሺህ ሄክታሩን ማስወገድ ተችሏል። አረሙ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ በየጊዜው የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ተወካይ ኀላፊ ተሬሳ ጨመዳ እንዳሉት በኢትዮጵያ ከ35 በላይ ወራሪ እና መጤ የአረም ዝርያዎች ተለይተዋል። ከዚህ ውስጥ አምስቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት እንደ ጣና ባሉ ሐይቆች ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ። አረሙ በብዝኀ ሕይዎት፣ በግብርና፣ በደን እና በዓሳ ሃብት ዘርፎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መኾኑን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከር ትኩረት ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ የወራሪ መጤ አረም ዝርያዎች አያያዝ እና ቁጥጥር ስትራቴጅን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የደቡብ ወሎ ዞን የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት እና የማኅበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ ጽጌ ገብረመድሕን እንዳሉት በደቡብ ወሎ ዞን 12 ዓይነት የመጤ ወራሪ አረም ዝርያዎች ተለይተዋል።

80 ሺህ ሄክታር የሚኾን መሬት በቅንጨ አረም፣ በአቅንጭራ፣ በወፍ ቆሎ ወራሪ አረሞች የተወረረ መሬት ተለይቷል ነው ያሉት። ሥርጭቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። ችግሩን ለመቅረፍ በታሰበው ልክ ባይኾንም እየተሠራ ነው ብለዋል።

ችግሩን አስመልክቶ በፌዴራል ደረጃ ትኩረት መሰጠቱ አረሙ የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ለመከላከል አቅም እንደሚኾንም ነው የገለጹት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሹዋሊድ በዓል በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሠራ ነው።
Next articleየሹዋሊድ በዓል አብሮነትን እና ወንድማማችነትን ለማጠናከር የሚያስችል በዓል መኾኑን የሐረሪ ክልል አስታወቀ።