
አዲስ አበባ: መጋቢት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም፣ የመቻቻል እና የአንድነት ምሳሌ የኾነችው የሐረር ከተማ የሹዋሊድ በዓልን ለማክበር ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው። የበዓሉን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በሐረር ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በፓናል ውይይቱ የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የሀረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌቱ ወዬሳ፣ የሀረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሱልጣን አብዱሰላም፣ የሀረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ ሙህየዲን አህመድ፣ የሀረሪ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሮዛ ዑመር፣ የአጎራባች ክልሎች የባሕል ቡድኖች፣ የሀረር ከተማ ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
የሹዋሊድ በዓል ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እንደሚከበር የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አንስተዋል። የሹዋሊድ በዓል የክልሉን ቱባ ባሕላዊ እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ብሎም በቱሪዝም ዘርፉ የክልሉን የቱሪስት ፍሰት ለማሳደግ ያለመ እንደኾነ አስረድተዋል።
የሹዋሊድ በዓል የሀረሬዎች ብቻ ሳይኾን የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴት መኾኑንም ተናግረዋል። በበዓሉ ልጃገረዶች፣ ወጣቶች፣ እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተው በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል ተብሏል። የቱሪስት መዳረሻ፣ የሥልጣኔ መናገሻ እና ጥንታዊ የንግድ ማዕከል የኾነችው የሐረር ከተማ በኮሪደር ልማቱ ደምቃ እና ተውባ በዓሉን ለማስተናገድ ዝግጁ መኾኗን አሚኮ በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ-ከሐረር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!