“ተደማምጦ እና ተመካክሮ መግባባት ላይ ከመድረስ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም” ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

48

ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን ጀምሯል። በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኢትዮጵያውያን በበርካታ ጉዳዮች ላይ በአንድ ልብ መክረን እና ተግባብተን እንደ አንድ ሕዝብ በተሰለፍንባቸው ጉዳዮች ላይ ታሪካዊ ድሎችን አስመዝግበናል ብለዋል።

በየዘመኑ የተነሱብንን ወራሪዎች አሸንፈናል፣ በአባቶቻችን ጥበብ፣ በእናቶቻችን ሀገር ወዳድነት እና ጸሎት፣ በወጣቶቻችን ጥንካሬ ዛሬም ባለ ሀገር ነን ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በሌላ ገጽታዋ እጅግ መሠረታዊ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለ መግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ጎልተው የሚታዩባት ሀገር ናት ብለዋል። የሃሳብ ልዩነቶች ለረጅም ዘመናት እየተዳራረቡ የመጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።

መሠረታዊ ሀገራዊ የሃሳብ ልዩነቶች እና መንስዔዎቻቸው ላይ ያልተግባባን መኾናችን ችግሩን የበለጠ የተወሳሰበ አድርጎብናል ነው ያሉት። የሃሳብ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን የምንፈታበት መንገድ ከምክክር ይልቅ የኅይል አማራጭ መኾኑ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፤ ዛሬም እያስከፈለን ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ በማሳያነት የሚጠቀስ እየኖርንበት ያለ እውነት ነው፣ የአማራ ክልል ሕዝብ በኢትዮጵያ የሀገር ምሥረታ እና ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ እሙን ነው፣ ለኢትዮጵያ መገለጫዎች የኾኑ የባሕል፣ የቅርስ እና የታሪክ ምሰሶዎችን ማቆም የቻለ ትልቅ ሕዝብ ነው ብለዋል።

እንደ እምነቱ ለፈጣሪው የተገዛ፣ ርህሩህ እና ለሀገሩ ቀናዒ የኾነ ሕዝብ ነው፤ በዚህም ሊመስገን እና ሊኮራ ይገባዋል ነው ያሉት። የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች እየሰፉ ስለመጡ፤ የሃሳብ ልዩነቶችን በኀይል አማራጭ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ይህ የተከበረ ሕዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፤ እየከፈለም ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ከሚናፍቋቸው የትምህርት ቤት ዳጃፍ መድረስ አልቻሉም፣ እናቶች እና እህቶቻችን በውስብስብ ችግር እንዲያልፉ ተገድደዋል፣ በርካታ ወጣቶች ሕልማቸውን ይዘው ለመቀመጥ ወይም ወደ ጫካ ለመግባት ተገድደዋል፣ ግምት የማይሰጠው ሃብት ንብረት ለውድመት ተዳርጓል፣ የማይተካ የሕይዎት ዋጋ ተከፍሏል፣ ይህ ሁነት በአንድ በኩል የአማራ ክልልንም ኾነ ሀገራችንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ያለ አንድ ሁነት ኾኖ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራዊ ምክክርን እጅግ አስፈላጊነት እና ወቅታዊነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ግጭቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ ተነጋግሮ፣ ተደማምጦ እና ተመካክሮ መግባባት ላይ ከመድረስ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ነው ያሉት። ለመመካከር ያልተግባባንባቸውን ጉዳዮች ሥረ መሠረት መለየት እና አጀንዳዎች ላይ መግባባት ይጠይቃል ብለዋል። ከምክክር ውጭ ያሉ አካሄዶች ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጡ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት አሳታፊ እና አካታች እንዲኾን በማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ወሳኝ ግብዓት እንደሚገኝበትም ተናግረዋል። በሚኖረው የምክክር ሂደት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን ታሪካዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደት አሳታፊነት እና አካታችነት በጽኑ ከማመን ባለፈ ሕጋዊ ግዴታው እንደኾነ በጽኑ ይገነዘባል ነው ያሉት። በክልሉ ያሉ ታጣቂ ወገኖችን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ተሳታፊዎች እንዲኾኑ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፣ አሁንም ሁሉንም አሸናፊ ወደሚያደርገው ምክክር እንዲሳተፉ ጥሩ እናቀርባለን ነው ያሉት።

በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ ይሄን ማድረግ መቻል ያሉብንን ችግሮች በምክክር ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ምን ድረስ እንደኾነ ማሳያ ነው ብለዋል። ላደረጉት የላቀ ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለኢትዮጵያ ሕመም ሕክምና የሚገኘው ከዚህ መድረክ ነው” ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ.ር)
Next articleየሹዋሊድ በዓል በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሠራ ነው።