“ለኢትዮጵያ ሕመም ሕክምና የሚገኘው ከዚህ መድረክ ነው” ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ.ር)

37

ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ጀምሯል። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በብዙ ችግሮች አልፈዋል ብለዋል። አሁን የሚያደርጉት ምክክርም እነዚህን ችግሮች ለይተው መፍትሔ ለማስቀመጥ እንደኾነም አስገንዝበዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በአማራ ክልል የተገኘው ይህን ችግር በምክክር ለመፍታት መደላድል ለመፍጠር እንደኾነ ነው ያብራሩት። ባለፉት ጊዜያት ለምን ተደማማን እና ለምን ችግር ውስጥ ገባን ብለን የምንጠይቅበት እና የምንመክርበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል። ኢትዮጵያውያን ሰከን ብለን በምክክር የምንጠያየቅበት ነው።

ይሄ መድረክ እንደ አንድ የሀገር ልጆች ደፍረን ለመደማመጥ የምንሞክርበት ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ለመዝመት እና ለመዋጋት እንደምንደፍረው ሁሉ ደፍረን ለመደማመጥ እና መፍትሔ ለማፈላለግ የምንሞክርበት ጊዜ ነው ብለዋል። ስንደማመጥ የተለያዩ እሳቤዎችን ወደ ጠረጴዛ አምጥተን የምንደማመጥበት ይኾናል ነው ያሉት።

ጊዜው በርህራሄ አንዱ የሌላውን ቁስል የምናይበት ነው፣ ወደ ውይይት አምጥተንም የጋራ መንገድ የምንፈልግበት ነው ብለዋል። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ራሳቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው ነው ያሉት። ለኢትዮጵያ ሕመም መድኃኒቱ የሚመጣው ከራሳቸው ከኢትዮጵያውያን እንደኾነም አስገንዝበዋል።ለኢትዮጵያ ሕመም ሕክምና የሚገኘው ከዚህ መድረክ ነው ብለዋል።

የጋራ ተስፋ እና ከፍታን የማዋለዱ ሂደት የሚመጣው ከምክክር መድረኩ እንደሚኾንም ጠቁመዋል። ምርጫችን የሰላም አማራጭ ነው። ለዚህም ምክክር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት ያከሰረንን ሂደት አንከተልም፤ በሚካሄደው ምክክርም በብቸኝነት ከፍ የምትለው ኢትዮጵያ ብቻ መኾኗን ነው ያብራሩት።

ያለን አማራጭ ግጭት ሳይኾን ሰላምን ማዋለድ ብቻ ይኾናል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በምክክር ጊዜ አሸናፊ እና ተሸናፊ የለም፤ ሁሉም አሸናፊ ነው” ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው
Next article“ተደማምጦ እና ተመካክሮ መግባባት ላይ ከመድረስ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም” ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ