
ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ ዛሬ ተጀምሯል።
በዚህ የአጀንዳ ማሠባሠብ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የተገኙት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ እንዳሉት የአማራ ሕዝብ እንደ ሀገር ለመምከር የሚያስፈልጉ አጀንዳዎችን ለማሠባሠብ ለተገኙ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ የአማራ ሕዝብ በምክክር መድረኩ በዚህ ልክ መሳተፉ እንዳስደሰታቸውም ነው የተናገሩት። ምክክሩ ትልቅ የሕዝብ ጉዳይ ነው በሚል ለተገኘው ሕዝብም ያላቸው አክብሮት ከፍ ያለ ስለመኾኑ አንስተዋል።
ባለፉት ዘመናት የቆየው ችግር በሀገሪቱ እድገት እና መጻዒ ሁኔታ ላይ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን የተናገሩት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ ሥላሴ ይህንም በምክክር ማስተካከል እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የትጥቅ ትግሎች ትንንሽ ድሎችን ሊያመጡ ቢችሉም ዘላቂ ሰላምን ግን ሊያመጡ እንደማይችሉ ነው የተናገሩት። ቁጭ ብለው በሀገር ጉዳይ ላይ መምከር ግን ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንደሚያግዝ ነው ያብራሩት።
“ዛሬ ለአማራ ሕዝብ ትልቅ ምዕራፍ ነው” ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ ይህም መቶ በመቶ እንደሚሳካ አልጠራጠርም ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ተሳታፊዎች እንደሚለዩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ተሳታፊዎቹ አጀንዳዎችን ከመለየት ባሻገር የአማራ ሕዝብን ወክለው በክልሉ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ የሚመክሩ ሰዎችን ለይተው እንደሚሰጡም ነው ያላቸውን ዕምነት የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!