
ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የሚያካሂደውን ክልል አቀፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ምክክር የመጨረሻ ፍቱን መድኃኒት ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ለዘመናት እርስ በእርስ በመደማማት አንዳች ያተረፈችው ነገር እንደሌላትም ተናግረዋል።
ሕይዎት ከመጥፋት፣ አካል ከመጉደል፣ ልጆቿ ሀገር ለሀገር ከመንከራተት፣ ከከፋ ድህነት እና ውድቀት ውጭ ያተረፈችው ነገር የለም ነው ያሉት። የመተላለቅ፣ የመጠፋፋት አዙሪት ለማስቆም ያስችላል ተብሎ የታመነበት ሀገራዊ ምክክር ተጀምሯል ብለዋል።
በዚህ ዘመን ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል። ምክክር የትልቅነት፣ የሥልጣኔ መገለጫ ነውም ብለዋል። ወንድም ወንድሙን ገድሎ ወንድነት የለም፣ ይህ የውድቀት ውድቀት ነው፣ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት፣ የሃይማኖት ሀገር ኾና እንዲህ ዓይነት ነገር ሲከሰት ያሳዝናል ነው ያሉት።
ምንም ነገር ሳናጣ ሁሉም ነገር ተሰጥቶን ስናበቃ የሁሉ ነገር ጭራ ነው የኾነው ያሉት ኮሚሽነሩ ይህ ነገር መቆም አለበት ብለዋል። በቃ ልንል ይገባል፤ ከዚህ ቀን ጀምሮ በኢትዮጵያ በየትኛውም ግዛት የሰው ደም መፍሰስ መቆም አለበት ነው ያሉት።
እናቶች የሚያለቅሱበት፣ ወላጆች ልጅ አልባ የሚኾኑበት ዘመን ማብቃት እንዳለበትም ተናግረዋል። በመነጋገር አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ማዋለድ እንችላለን ነው ያሉት። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንደኛው ዓላማ በምክክር ያለው አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት፤ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት መገንባት ነው ብለዋል።
የምክክር ሂደት የሰላም ሂደት ነው፤ ፈጣሪ የሚወደው ሂደት ነው፤ ይሄን አምናችሁ በመምጣታቸው ደስ ብሎናል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ከፍ ብላ የምትታይበት ቀን ሩቅ አይኾንም፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፈርጥም ትኾናለች ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን