“የሸዋል ኢድ ሐረር የምትታወቅበት የአብሮነት እና የመቻቻል እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው” አቶ አደም ፋራህ

16

ባሕርዳር: መጋቢት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የሸዋል ኢድ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አሥተላልፈዋል።

አቶ አደም ፋራህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ውብ እና አስደናቂ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል እና እሴቶች ባለቤት ናት ብለዋል። ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በቀረጽነው የለውጥ ፍኖተ ካርታ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ጥልቅ የሆኑ የማኅበራዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት የማኅበራዊ ልማታችንን ማጠናከር እና በሀገራችን ያሉ የቱሪዝም ጸጋዎችን በማልማት የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ መገንባት ተጠቃሽ ናቸው ነው ያሉት።

በዚህ የለውጥ ዓመታት ጉዞ ውስጥ በበርካታ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የሕዝባችንን መልካም እሴቶች የሚያጠናክሩ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚያስችሉ ባሕሎቻችን እና እሴቶቻችንን በማጎልበት ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ብለዋል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የሸዋል ኢድ ባሕላዊ ክብረ በዓል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።

የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ የኾነው፣ የተዋበ ገፅታን የተላበሰው የሸዋል ኢድ አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች የማይዳሰስ ቅርስ ኾኖ መመዝገቡን ነው የተናገሩት። በዓሉ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን በማጎልበት ጠቀሜታው የጎላ መኾኑንም ገልጸዋል።

የሸዋል ኢድ ሐረር የምትታወቅበት የአብሮነትና የመቻቻል እሴትም ጎልቶ የሚታይበት፣ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችም በጋራ የሚሳተፉበት ባሕላዊ ክብረ በዓል ነው ብለዋል።

በቀጣይ እንደ ብልጽግና ፓርቲ ባሕላዊ ቅርሶቻችን እና ሌሎች ጥልቅ ማኅበራዊ ሀብቶቻችን ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ እና ለሀገራችን ተገቢውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲሰጡ ይበልጥ አጠናክረን መሥራታችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

እንኳን ለሸዋል ኢድ በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የሚያካሂደውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ዛሬ ይጀምራል።
Next article“ምክክር የመጨረሻ ፍቱን መድኃኒት ነው” ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም