
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ባህላዊ መድኃኒት ሕክምና አዋቂዎች ማኅበር ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ይጠቅማሉ ያላቸውን 58 ዓይነት የባህል መድኃኒቶች ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስረከበ፡፡
ማኅበሩ ለበሽታው ፈውስ ሊሰጡ ይችላሉ ያላቸውንና በመጀመሪያ ዙር ወደ ላብራቶሪ ገብተው ተጨማሪ ፍተሻና ምርምር የሚደረግባቸው 25 ዓይነት ባህላዊ መድኃኒቶችንም በመለየት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ለኢንስቲትዩቱ አስረክቧል፡፡
ከቀረቡት የባህል መድኃኒቶች ውስጥ በሕመሙ ላልተያዙ ሰዎች መከላከያ የሚሆኑ 13 ዓይነት መድኃኒቶችና በሕመሙ ለተያዙ ሰዎች ሊሆኑ የሚችሉ ደግሞ 45 ዓይነት መድኃኒቶች በጥቅሉ 58 ዓይነት መድኃኒቶች ይገኙበታል፡፡
መድኃኒቶቹ በመከላከያ መልክ የቀረቡ፣ በተለያዬ መልክ የሚሰጡና ወደ ሆድ የሚገቡ ተብለው የተከፋፈሉ ናው፡፡ ከዚህ በፊት በጤና ሚኒስቴር በኩል በተሰጠ መመሪያ መሠረት ዛሬ በምድብ አንድ ወደ ላብራቶሪ የሚገቡ መድኃኒቶች ኮድ በማኅበሩ የተሰጣቸው ሆነው የቀረቡ ስለሆነ ቀጣይ ምርመራ ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ባህላዊ መድኃኒት ህክምና አዋቂዎች ማኅበርን በመወከል የባህል ሀኪም አቶ ታደሰ ወልደገብርኤል በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተመራማሪና የባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒቶች ምርምር ዳይሬክተር ፍሬሕይወት ተካ አስረክበዋል፡፡
በርክክቡ ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳው (ዶክተር እና የባህል ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዲኤታ ብዙነሽ መሠረት ተገኝተዋል፡፡
ምንጭ፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር