
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ የጀመረችው ብዝኃ ዘርፍ ሪፎርም አረሙን ከስንዴው እየለየ በአስደናቂ የስኬት መንገድ በመፈጸም ላይ ይገኛል ብለዋል።
የሀገራዊ ለውጡን ሰባተኛ ዓመት ስኬታማ ጉዟችንን እያከበርን ባለንበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት “ልህቀት በሰው ተኮር አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት የፌደራል ከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች ተሞክሮ ተኮር ሥልጠና ዛሬ አስጀምረናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያውያን የዘመናት መሻት የሆነውን የተሳለጠ የመንግሥት አገልግሎትና አሥተዳደር ሥርዓት ለመገንባት እና በጽኑ መሠረት ላይ ለማኖር የሚያስችል ሪፎርም እያካሄድን ነው።
ሪፎርሙ ለአፍሪካ ተምሳሌት የምትሆን፣ የበለጸገችና ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት እና የሕዝባችንን የአገልግሎት ፍላጎት ለማርካት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ይህንን ታሪካዊ ምዕራፍ በማሳካት ዘመን ተሻጋሪና ጠንካራ የመንግሥት የአገልግሎት ሥርዓት ለመዘርጋት ሁሉም የመንግሥት መሪ እና ሠራተኛ በሚጠበቅበት ደረጃ መትጋት ይኖርበታል ነው ያሉት።
ይህ ተሞክሮ ተኮር ሥልጠና የሚካሄደው የመንግሥት አገልግሎትና አሥተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት በሚያስችሉ በጸደቁ እና በረቂቅ ደረጃ ባሉ ሰነዶች መኾኑንም ገልጸዋል።
በሂደቱም የእስካሁን የሪፎርሙ አፈጻጻም የደረሰበት ደረጃ፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!