
አዲስ አበባ: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው 1 ዓመት ብቻ 2 ነጥብ 85 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ተኪ ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት ስለመቻሉ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገልጸዋል። ዘርፉ የሚያጋጥመውን ችግር እየፈቱ ፈጣን እድገት እንዲመጣ የሚያስችል አሠራር ኢትዮጵያ እየተከተለችም ነው ብለዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል። አምራች ዘርፉ እንደሀገር ኢኮኖሚን ለማሻገር ቅድሚያ ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች አንዱ ነው ብለዋል። ይህም በፖሊሲ ጭምር ተደግፎ መመራቱ ለውጥ እንዲመጣ አድርጎታል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።
ከዚህ በፊት መንግሥት መር የነበረው የዘርፉ አሠራር በአኹኑ ጊዜ በፖሊሲ ደረጃ የግሉ ዘርፍ መር አካሄድን እየተከተለ ነው ብለዋል። በፋይናንስ አቅርቦት፣ በኀይል እና መሬት አቅርቦት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷልም ብለዋል። በተለይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያለበትን ችግር የሚፈታ አሠራርን ከመከታተል ባለፈ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የሚመራ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል የዘረፉን ማነቆ በፍጥነት እየፈታ ነው ብለዋል።
በእነዚህ ክትትሎች እና ትኩረቶች ምክንያት አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ባለፈው ዓመት 10 በመቶ አድጓል ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ ከዚህ በላይ ይጠበቃል። እንደ አቶ ታረቀኝ ገለፃ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ43 ወደ 60 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። በተያዘው የተኪ ምርት ስትራቴጂ መሰረት ባለፈው ዓመት ብቻ 2 ነጥብ 844 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ዘርፉ አምርቷል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ከ10 ዓመት በኋላ 5 ሚሊዮን ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ማቀዱን ሚኒስቴር ዴኤታው ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን