
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መጋቢት 24 የትልሞቻችን ሁሉ የስኬት ጫፍ መጀመሪያ፣ የለውጥ ጮራ መባቻና የብልጽግና ዘመን ጅማሮ ነው ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ያለፉት የለውጥ ዓመታት አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ሰባት የለውጥ ዓመታትን በድል ተሻግረን የሰነቅናቸውን ታላላቅ ሕልሞች እያሳካን፣ የገጠሙንን ፈተናዎች ከሕዝባችን ጋር በቅንጅት በመሥራት እየተሻገርን፣ የመዳረሻ ተስፋዎቻችንን ወደ ሚጨበጥ ብርሃን እየቀየርን እና ለሕዝባችን የሚበጁ አያሌ ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን ነው ያሉት።
መጋቢት 24 የትልሞቻችን ሁሉ የስኬት ጫፍ መጀመሪያ፣ የለውጥ ጮራ መባቻና የብልፅግና ዘመን ጅማሮ ነው ብለዋል። በብልጽግና ዘመን ስብራቶቻችንን የሚጠግኑ፣ የምናባችንን ከፍታና የተስፋዎቻችን ጥልቀት የሚመጥኑ የለውጥ ሥራዎች ጥልቀትና ጥራት ባለው መልኩ በከተማና በገጠር እየተከናወኑ ናቸው ነው ያሉት።
መዳረሻዎቻችን ከመንገዶቻችን ጋር የተሰናሰሉ፣ የሕዝባችንን ዘላቂ ተጠቃሚነት መረጋገጣቸውን የሚመሰክሩ የለውጥ አሻራዎች ሕያው ማሳያ ከተሞቻችን መካከል ደግሞ ደሴ አንዷ ናት ብለዋል።
በደሴ ከተማ ከቧንቧ ውሃ አደባባይ እስከ ወሎ ባሕል አምባ የሚደርስ 1 ነጥብ 89 ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 46 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው የኮሪደር ልማት፣ ቅልጥፍናና ጥራትን የሚጨምር፣ አገልግሎትን የሚያሳልጥ እና ደህንነትን የሚያስጠብቅ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክትና ሌሎችም ተጠቃሽ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!