
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አግኝቶ ማጥት ደርሶባታል። አጥቶ ማግኘትንም እንዲሁ። በ2007 ዓ.ም የሥራን ሀ ሁ… ስትጀምር በደብረታቦር ከተማ የደመቀ ሽሮ ቤት ነበራት እናኑ ደሴ። ከራሷ ተርፋ ዘመዶቿን ታግዝ ነበር። እንደ ሥራዋ የፈካው ወጣትነቷም በብዙዎች ዘንድ አስወደዳት። ሥራዋን በደስታና እና በጥሩ መንፈስ እየሠራች ትዳር የመያዝ ሃሳብ መጣ። ውኃ እንዲያጣጣት፣ ሥራ እንዲያግዛት፣ የሕይወት አጋር የሚኾናት፣ አንድ አካል አንድ አምሳል የሚኾናትን ታገባ ዘንድ ወደደች። አገባችም።
መኖሪያቸውን ዳንሻ ከተማ አድርገው በሥራ ተጠመዱ። ሥራቸው ያማረ ገቢያቸውም መልካም ኾነ። በመካከል ሕይወትን የበለጠ በሚያስውብ በልጅ በረከት ታደሉ። ጥንዶቹ ዳንሻ ከተማ ለቅቀው ለሥራ ወደ ጎንደር ለመሄድ ተስማሙ። ጊዜው 2010 ዓ.ም ነበር። ነገር ግን እርሷ ወደ ጎንደር ስትሄድ ባለቤቷ ሳይከተላት ቀረ። ትዳር ፈረሰ። ሕይወት ሌላ መልክ ያዘች። ብቻዋን ልጅ ማሳደግ ቸገራት። ሌላ የሕይወት አጋር ታገባ ዘንድ ፈቃዷ ኾነ። ባል አግብታ ወደ አዲስ አበባ አቀናች። ከሁለተኛው ባሏም ልጅ ጸነሰች።
ባለታሪካችን እናኑ ደሴ እንደ መጀመሪያው ሁሉ በሁለተኛው ትዳሯም ፈተና ገጠማት። ሕይወት ከበደቻት። የባሏ እንክብካቤ እስከዚህም ኾነባት። ነፍሰ ጡርም ኾና ለመኖር መብላት ስላለባት በሰው ቤት በተመላላሽነት ትሠራ ነበር። የምግብ ዝግጅት እና ጸጉር ሥራም ሠልጥና ሞክራዋለች። ጌጦቿን እስከ መሸጥ ያደረሳት የኑሮ ክብደት ደረሰባት። ሕይወት የከበደቻት እናኑ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕርዳር አቀናች።
ገጠር ወደ ሚገኙ ቤተሰቦቿም ሄዳ በመውለድ ሕጻኗን አጠነከረች። ከዚህ ወደ ባሕርዳር ተመለሰች። እንደምንም ቤት ተከራይታ የሚበላ ከደብረታቦር ገጠራማ አካባቢ እያመላለሰች ለሥራ ፍለጋ በባሕር ዳር ጎዳናዎች እና ቤቶች ተዘዋወረች። ለልጆቿ ዳቦ መግዣ የጠፋበት ጊዜም ነበር። የሁለት ዓመቷን ልጅ ወደ አያቶቿ መላክንም በመፍትሔነት ተጠቅማለች።
በመንከራተት ጊዜዬ፣ ጉልበቴ እና ትዕግስቴ እያለቀ ስለነበረ በኾነ ባልኾነው እነጫነጫለሁ። ራሴን ለማጥፋትም አስቤ ነበር የምትለው እናኑ ከዕለታት በአንድ ቀን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሕይወቷን የለወጠ ዕድል እንደፈጠረላትም ትናገራለች። ችግሯን የተረዱ ሰዎች በሰጧት ጥቆማ መሠረት ከመምሪያው ሄዳ ብሶቷን ተናገረች። ብሶቷም ተሰማ።
መጀመሪያ ስንገናኝ በሥነ ልቦና ተጎድታ ነው ያገኘናት ያሉት የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ምክር ተሰጥቷት እንድትረጋጋ መደረጉን አስታውሰዋል። ለተጋላጭ ሴቶች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ እና የብድር ተጠቃሚ እንድትኾን አደረግን። የልብስ ስፌት መኪና ተገዝቶላት እና መሥሪያ ሼድ ተሰጥቷት በ2016 ዓ.ም ሥራ እንድትጀምር ተደረገ ነው ያሉት።
አሁን ላይ በልብስ ስፌት እና ጫማ ሠርቶ በመሸጥ የምትተዳደር ሲኾን ሌሎች ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችንም ትሠራለች። የስፌት ክር ችርቻሮ፣ የሹራብ ጫማዎችን ሠርቶ መሸጥ፣ አምባሻ፣ ድፎ ዳቦ እና ፒዛ በትዕዛዝ በማዘጋጀትም ትሸጣለች። እናኑ በተደረገላት ድጋፍ በፍጥነት ሥራ ጀምራ መለወጧን የተናገሩት ኀላፊዋ እሷም በበኩሏ ሥልጠና ሰጥታቸው ሥራ የጀመሩ ወጣቶች መኖራቸውን ነው የገለጹት።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እንደ እናኑ አይነት ሴቶችን ችግር ለመቀነስ 56 ሺህ ሴቶች በልማት ኅብረት ተደራጅተዋል። በአትክልት ልማት፣ በልብስ ስፌት እና በሱቅ ሥራ መሰማራታቸውን ኀላፊዋ ተናግረዋል። ለሥራ ማስጀመሪያም 5 ሚሊዮን 110 ሺህ ብር መሰጠቱን ተናግረዋል።
ሴቶች በማኅበር ተደራጅተው 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር መቆጠባቸውንም ጠቅሰዋል። ለ520 ሴቶችም ብድር ተሰጥቷል ነው ያሉት። የሴቶችን የምጣኔ ሀብት አቅም በማሳደግ ችግሮቻቸውን ከመቀነስ ሥራው በተጨማሪ የሕግ ድጋፍ እና የጎልማሳ ትምህርት በማመቻቸት እየተሠራ መኾኑን ነው ኀላፊዋ የተናገሩት።
የተሻለ ገበያ ያለው የሥራ ቦታ ስታገኝ የልብስ ዲዛይነር መኾን የምትፈልገው እናኑ ያንን ሁሉ መንከራተቷን ያስታገሱላትን ሁሉ ታመሠግናለች። ”ከችግር ውስጥ ነው መዘው ያወጡኝ ትላለች። ሕይወት ትግል ነውና እናኑም ሕይወትን ለማሻሻል በሌላ የትግል ምዕራፍ ላይ ናት፤ በአዲስ ተስፋ እና በአዲስ የሥራ መንፈስ። በጥረቷ እና በሰዎች እገዛ ከችግሯ ወጥታ የተሻለ ሕይወት እየፈጠረች ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!