
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ የሚያደርገውን የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በአማራ ክልል የተካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ ከተጠበቀው በላይ ነው ብለዋል። አርሶአደሮች፣ ነጋዴዎች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ሀሳባቸውን በነጻነት እና በተደራጀ መንገድ እንዳነሱም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ ሁኔታዎችን የተረዳ፣ ያወቀ እና በጥልቅ ሥነ ምግባር የታነጸ ነው ብለዋል። ሀገሩን የሚወድ፣ ልዩነትን የሚጠላ፣ ስለ ሌላው የሚያሳስበው ሕዝብ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የተካሄደው ልየታ በነጻነት እና በገለልተኝነት ነው ብለዋል። የማንም ጣልቃ ገብነት እንዳልታየበትም ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም የማንም ጣልቃ ገብነት አይፈቅድም ነው ያሉት። ቀደም ሲል የነበሩ እና ሕዝብ በበቂ ሁኔታ አልተወከልኩባቸውም ሲላቸው የነበሩ ጥያቄዎች እንዳይኖሩ ለማድረግ እስከታች ድረስ ወርደን አሳትፈናል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ በሕግ መንግሥቱ አልተሳተፍኩም፣ አልተወከልኩም የሚል ጥያቄ እንደሚያነሳ የተናገሩት ኮሚሽነሩ አሁን ላይ ያ ጥያቄ እንዳይኖር እስከታች ድረስ በነጻነት እና በገለልተኝነት አሳትፈናል ነው ያሉት።
ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ተፈናቃዮችም ተሳትፈዋል ብለዋል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበት ምክንያት ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት መኾኑንም ተናግረዋል። እንደ ሀገር ሀገራዊ መግባባት ያስፈልገናል ብለዋል። እጅግ መሠረታዊ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች አልተግባባንም፣ የሀሳብ ልዩነቶች አሉን ያሉት ኮሚሽነሩ ልዩነቶች ደም ሲያፋስሱን ኖረዋል፣ በቃ ልንል ይገባል፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመው ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የየትኛውም አካል ወገን አለመኾኑን እና ወገንተኝነቱ ለመላው ኢትዮጵያውያን መኾኑንም ተናግረዋል። ሀገር ከችግር ወጥታ ለመጭው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ማስረከብ ነው የምክክሩ ዓላማ ብለዋል።
መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል። “ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት መፍታት፣ የንግግር እና የምክክር ባሕልን ማሳደግ ይገባል” ነው ያሉት። አስተማማኝ ሰላም እንደ ሀገር ማጽናት፣ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት መገንባትም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ቁጭ ብሎ በመመካከር አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር፣ ችግሮችን መፍታት፣ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ ዲሞክራሲን ማስፈን ከሁሉም እንደሚጠበቅም አንስተዋል። ግጭት ከኪሳራ ውጭ ጥቅም እንዳልተገኘበት ነው የተናገሩት። ኪሳራውም የሰው ሕይዎት መኾኑን ነው የገለጹት።
የግጭት እና የጦርነት አስተሳሰብ ሊበቃ እንደሚገባም ተናግረዋል። ሁላችንም ግጭት እና ጦርነት ይብቃ ብለን መጮህ አለብን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
