“በመጠላለፍ ሳይኾን በመደጋገፍ የቀውስ ጊዜን ማለፍ ያስፈልጋል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው

18

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ያለፉት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሟል። በሥራ አፈጻጸም ግምገማው መልዕክት ያስተላለፉት ‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው ባለፉት ወራት በከተማው የነበረውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሰፊ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።

በኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ በመቀየር የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሁንም ያልተነኩ በርካታ ተግባራት መኖራቸውን አብራርተዋል። በቀጣይ አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን፣ ሕገ ወጥ ተግባራትን መከላከል እና የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቃል ነው ያሉት።

“በመጠላለፍ ሳይኾን በመደጋገፍ የቀውስ ጊዜን ማለፍ ያስፈልጋል” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለዚህ ደግሞ መነጋገር እና ለመፍትሔው መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለይቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። ‎ባለፉት ወራት በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ መማር ማስተማርን ማስቀጠል መቻሉ፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ እና ሸማች እና ሻጭን ለማገናኘት በከተማው የተጀመረው የገበያ ማዕከል ግንባታ የውይይቱ ተሳታፊዎች በጥንካሬ ያነሷቸው ጉዳዮች ናቸው።


‎ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በታቀደው ልክ አለመሥራት፣ አገልግሎት አሠጣጡን ማዘመን አለመቻል እና ከብልሹ አሠራር ጸድቶ ተገልጋይን በአግባቡ የሚያገለግል የሲቪል ሰርቪስ ሙያተኛ የሚፈጥር መሪ አለመገኘት ሌላው በግምገማው በውስንነት የተጠቀሱ ተግባራት ናቸው። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮነን ያሉ ውስንነቶችን በማረም በቀሪ ወራት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።


‎በቂ አገልግሎት በማይሰጡ የሥራ ኀላፊዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዲሲፒሊን ርምጃ ከመውሰድ እስከ ኀላፊነት ማንሳት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ‎የታየውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ፣ የተጀመሩ መሠረተ ልማቶችን እና ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በቀጣይ የሚሠሩ ተግባራት መኾናቸውም በውይይቱ ተነስቷል።

ዘጋቢ:-አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአጀንዳ ማሠባሠብ ምዕራፍ አጀንዳዎች የሚለዩበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው”
Next article“ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በምክክር መፍታት ይገባል”