“የአጀንዳ ማሠባሠብ ምዕራፍ አጀንዳዎች የሚለዩበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው”

24

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ የሚያደርገውን የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ናቸው የሰጡት።

በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የምክክር ሂደቶችን ለማከናወን የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል። ባለፉት ጊዜያት በክልሉ 267 ወረዳዎች 10 የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወክለው የተመለመሉ ከ4ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች የተለዩባቸው መርሐ ግብሮችን መከናወናቸውን አንስተዋል።

ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታ መርሐ ግብርን ማጠናቀቁን ተከትሎ ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 4/2017 ዓ.ም ድረስ የክልሉን የአጀንዳ ማሠባሠብ የምክክር ምዕራፍ እንደሚያከናውን ገልጸዋል። በዚህ መርሐግብር ከክልሉ የምክክር ባለድርሻ ከኾኑት ከኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከተቋማት እና ማኅበራት የተወከሉ በጥቅሉ ከ6ሺህ በላይ ወኪሎች ይሳተፋሉ ብለዋል።

በዚህ የምክክር ምዕራፍ በክልሉ ከሚገኙ 267 ወረዳዎች 10 የማኅበረሰብ ክፍሎችን የወከሉ ከ4ሺ 500 በላይ የኅብረተሰብ ወኪሎች በመጀመሪያዎቹ አራት ቀናት በአጀንዳ ሀሳቦቻቸው ላይ ውይይት በማድረግ ክልላዊ እና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች ያጠናቅራሉ ነው ያሉት።

በሚቀጥሉት ቀናት ደግሞ ተመራጭ የኅብረተሰብ ወኪሎችን ጨምሮ የመንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የተቋማት እና ማኅበራት ወኪሎች በአጀንዳዎቻቸው ላይ በመወያየት ክልላዊ እና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች አጠናቅረው ለኮሚሽኑ ያስረክባሉ ተብሏል።

ይህ መርሐ ግብር የክልሉ የምክክር ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸውን አጀንዳዎች የሚለዩበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል። የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ በእጅጉ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል። የተመረጡ ባለድርሻ አካላት ወኪሎች የምክክሩን ክልላዊ እና ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለሂደቱ ስኬት በተለያየ መስክ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ አካላትን አመሥግነዋል። እስከ ምክክሩ ፍፃሜ ድረስ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል። ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲወከል ጥረት ሲደረግ መቆየቱን እና አኹንም ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል ሀሳብ የሚወከልበትን አውድ ማመቻቸታቸውንም ተናግረዋል።

የትኛውም ወገን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አልተወከልኩም እንዳይል እንዲወከል ጥረት አድርገናል ነው ያሉት። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አካሄድ አጋር አካላትን ያሳተፈ መኾኑንም ተናግረዋል። አጀንዳ ያላቸው ወገኖች ሁሉ አጀንዳዎቻቸውን ማቅረብ ይችላሉ ነው ያሉት። በተለያዩ አማራጮች መሳተፍ እና አጀንዳቸውን ማቅረብ እንደሚችሉም ተናግረዋል። በተደረጉ ውይይቶች ወካይ የኾኑ ሀሳቦች ተነስተዋልመሸ ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሚሊዬነሯ አርሶ አደር”
Next article“በመጠላለፍ ሳይኾን በመደጋገፍ የቀውስ ጊዜን ማለፍ ያስፈልጋል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው