አዲስ አበባ: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ፈትያ መሐመድ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ባብሌ ወረዳ ኤረር ጉዳ ቀበሌ ነዋሪ ናት። ባለፉት ዓመታት በአረብ ሀገር ለረጅም ጊዜ መኖሯን፣ በኋላም በሀገሯ በግብርና ዘርፍ ተሠማርታ ለመለወጥ አቅዳ ወደ ሀገሯ መመለሷን ነው አጫወተችን።
በ2002 ዓ.ም በትውልድ ቦታዋ ባብሌ ወረዳ በአትክልትና ፍራፍሬ ሥራ መሠማራቷን ታስታውሳለች። መንግሥት በሠጣት በ54 ሄክታር መሬት ላይ 40 ሺህ በላይ የማንጎ፣ ፓፓያ፣ አቦካዶ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ቡና እና ሌሎች ቋሚ አትክልቶችን እያለማች ትገኛለች። ሥራውን በጀመረች ስድስት ዓመት ምርት ማግኘት መጀመሯን ነው የጠቆመችው። ከቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ልማቱ በተጨማሪም የወተት ላሞችን እያረባች ትገኛለች።
የወተት፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾኗን ወይዘሮ ፈትያ ተናግራለች። ሴትነት በግብርና ዘርፍ ተሠማርቶ ለመለወጥ አያግድም የምትለው ወይዘሮ ፈትያ ዛሬ ላይ ከ500 ሚሊዮን በላይ ካፒታል መድረሷን ገልጻለች። በሥራዋም ከ40 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች።
ምሥራቅ ሀረርጌ ዞን የዝናብ እጥረት ያለው እና ወጣ ገባ የመሬት አቀማመጥ በመኾኑ ለማልማት ፈታኝ እንደነበር የምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ዋና አሥተዳደር ምስጊ መሐመድ ገልጸዋል። በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ ለችግር እና ለስደት ሲዳረግ ነበር ብለዋል። ችግሩን ለመፍታትም ዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ እያከናወነ ይገኛል። አኹን ላይ በተሠራው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ሥራም የተራቆተው መሬት መልሶ እንዲያገግም፣ የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጨምር፣ የአፈር ለምነት እንዲጨምር፣ የወንዞች ውኃ መጎልበት ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በዚህም በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት መጀመሩን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ተፋሰሶች የማር ምርት ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ማምረት ተችሏል። እንደ ዋና አሥተዳዳሪዋ ገለጻ የሰው ኀይል እና የተፈጥሮ ሀብትን አሟጦ በመጠቀም የሌማት ትሩፋት እና የበጋ መስኖ በስፋት እየተተገበረ ይገኛል።
በእነዚህ ዘርፎችም ከዩኒቨርሲቲ እና ከኮሌጅ የወጡ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ማሰማራት ተችሏል። በዞኑ 75 ሺህ አባላት ያሉት ከ800 በላይ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። በእነዚህም ከ700 በላይ ሸዶችን ሠርተው ማስረከባቸውን ዋና አሥተዳዳሪዋ ገልጸዋል። በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶችም ከፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት ተመቻችቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ብቻ 190 ሚሊዮን ብር መስጠት ማቻሉን ነው ያነሱት። የኑሮ ውድነትን ለማቅለል እና ከጥገኝነት ለመውጣት ባለፉት ሦሥት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎችም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪዋ። ባለፉት ሁለት ዓመታት በዞኑ ከ66 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እየለማ መኾኑንም ገልጸዋል። በ17 ወረዳዎች ከ2 ሚሊዮን በላይ ሙዝ፣ ከ1 ሚሊዮን በላይ አቦካዶ መልማቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከ25 ሺህ በላይ ወጣቶች እና አባዎራዎች መሠማራታቸውን ነው አሥተዳዳሪዋ ያነሱት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን