“ሰው ከሚጎድለው ገንዘቡ ቀንሶ የተቸገሩትን ያግዛል፤ ገንዘብ በሁላችን ላይኖር ይችላል፤ ደም ግን በሁላችን አለ…’’ የአልማ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ

154

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የዋናው ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች በቢሯቸው ደም ለግሰዋል፡፡ ደም የለገሱት ከ30 በላይ የተቋሙ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ናቸው፡፡

የአልማ ራዕይ በክልሉ የራሱን የልማት ችግሮች በራሱ አቅም የሚፈታ ማኅበረሰብ ተፈጥሮ ማዬት ነው፡፡ የማኅበሩ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መዝገበ አንዷለም እንዳሉት ልማት ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ቢሆንም ሕዝብ በቀላሉ አዋጥቶ መፍታት ይቻላል፡፡ ነገር የማኅበረሰብን ጤና መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡ ፡በደም እጦት የሚሰቃዩ እና ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቀላል አይደሉም፡፡ የብዙዎች ችግር የሆነውን የደም እጥረት ብዙዎች ተሰባስበው በቀላሉ ሊፈቱት እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡

“ሰው ከሚጎድለው ገንዘቡ ቀንሶ የተቸገሩትን ያግዛል፤ ገንዘብ በሁላችን ላይኖር ይችላል፤ ደም ግን በሁላችን ስላለ ምንም ሳይጎድልብን በደም እጦት ለተቸገሩ መድረስ የሚሰጠን ውስጣዊ ሀሴት ከፍተኛ ነው” በማለት ደም መለገስ ገንዘብን ወይም ቁስን ከመስጠት በተለዬ ሕይወትን ለማትረፍ የሚበረከት ውድ ስጦታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አልማ በደም ዕጥረት ምክንያት የሚሰቃዩና ሕይወታቸውን የሚያጡ በርካቶች መሆናቸውን በመረዳት በጎ ፈቃደኞች ደም እንዲለግሱ እየቀሰቀሰም ነው፡፡ የአልማ አባላት ልማትና የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት ዳይሬክተር ጌቴ ሙላቱ እንዳሉት በርካርታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ደም ለመለገስ ፈቃደኛ ሆነው ኮሮና ወረርሽኝን በመፍራት ላይሰጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከመፍራት ይልቅ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዴት እና በምን መልኩ ደም መስጠት እንዳለባቸው ከደም ባንክ ጋር በመነጋገር ለመሥራት ማሰቡንም ተናግረዋል፡፡

አልማ የክልሉን የልማት ችግር ለመፍታት እያከናውናቸው ካሉ ዐበይት ተግባራት ባለፈ የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር እየሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የደም እጥረት ችግሩን ለመፍታት በዕቅድ እየሠራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

አልማ በክልሉ 150 ወረዳዎች እና በሁሉም ቀበሌዎች ለበጎ ፈቃደኞች ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ በየቅርንጫፉ ያሉ ሠራተኞቹ ደም እንዲለግሱ መግባባት ተፈጥሯል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን እና ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ ለኮሮና ቫይረስ መከላከልና ሕክምና ሊያግዙ የሚችሉ 58 የባህል መድኃቶች ለኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፍተሻ ተሰጡ፡፡