በየሁለት ሰከንዱ አንድ ሰው የሚቀጥፈው በሽታ!

112

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ስትሮክ ጭንቅላት ውስጥ ያሉ ሴሎች ኦክሲጅን እንዳያገኙ በማድረግ እና በሰውነት ውስጥ በቂ የደም ዝውውር እንዳይኖር በማድረግ የሚከሰት ሕመም ነው። ስትሮክ በዓለም ላይ በየሁለት ሰከንዱ አንድ ሰው በስትሮክ ሕመም ይጠቃል።

የአካል ጉዳት እና ሞትን ከሚያስከትሉ በሽታዎች አንዱ በመኾኑ እጅግ በጣም አሳሳቢ እየኾነ መጥቷል። ስትሮክ ሁለት አይነት ሲኾን አንደኛው በጭንቅላት ውስጥ ደም ሲፈስ ወይም የደም ሥሮች ተጎድተው ደም ወደ ውጭ በመፍሰሱ ምክንያት የሚከሰት በሽታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የደም ዝውውር ሲገታ ወይም መተላለፍ ሳይችል ሲቀር እና በቂ ኦክሲጅን ወደ ሰውነት መዘዋወር ባለመቻሉ ምክንያት የሚከሰት አይነት ነው።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የልብ እና የደም ሥር በሽታዎች ፕሮግራም አሥተባባሪ ሞላ ገደፋው (ዶ.ር) እንዳሉት ስትሮክ ለአዕምሮ የሚደርሰው የደም ሥር ከልክ በላይ በመጥበብ ወይንም የደም ሥር በመፈንዳት ለተወሰነው የአዕምሮ ክፍል ባለመድረስ የሚፈጠር ነው። በሽታው ለከፍተኛ ሕይወት መጥፋት እንደሚያደርስም ነው የገለጹት። ከሞት የተረፉት ደግሞ በቋሚነት በሚባል ደረጃ የሰውነት አለመንቀሳቀስ፣ መስነፍ፣ መዛል፣ የፊት ክፍል መጣመም ወይንም መዞር ያስከትላል።

በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነቱ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። በዓለም በዓመት እስከ 90 ሚሊዮን የሚኾኑ ሰዎች በስትሮክ ይጠቃሉ። ከዚህ ውስጥ እስከ 5 ሚሊዮን የሚኾኑ ሰዎች ይሞታሉ። ሌሎቹ ደግሞ ለኑሯቸው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ኾነው ቀሪ ዘመናቸውን ይኖራሉ። ከ20 ዓመት በፊት አንድ ሰው ተላላፊ ካልኾኑ በሽታዎች ጋር የሚያሳልፈው የዕድሜውን 20 ከመቶ ብቻ ነበር።

ያ ማለት አንድ ሰው 100 ዓመት ቢኖር 80 ዓመቱን ያለምንም ተላላፊ በሽታ ይኖር ነበር። በፈረንጆቹ አቆጣጠር የ2020 መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በዓለም ላይ የሰው ልጅ 70 ከመቶ የሚኾነውን ዕድሜውን ተላላፊ ካልኾኑ በሽታዎች ጋር ያሳልፋል። ችግሩ ይበልጥ የሚጎላው ደግሞ የጤና ሥርዓታቸው ደካማ በኾኑ የአፍሪካ ሀገራት በተለይም ደግሞ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ነው።

በእነዚህ ሀገራት ደግሞ በሽታው በግለሰብ፣ በቤተሰብ አልፎም እንደ ሀገር ማኅበራዊ ምስቅልቅል እና ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት እያስከተለ ይገኛል። አሥተባባሪው እንዳሉት በአማራ ክልል ምን ያህል ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን እንደሚያጡ ማወቅ ባይቻልም በርካታ ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት ሳይደርሱ በቤታቸው ሕይወታቸውን ያጣሉ።

በሆስፒታሎች ሕይወታቸው ከሚያጡ ሰዎች መረጃ ተወስዶ ሲታይ ግን በስቶሮክ የሚሞቱት የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል። በዚህም በክልሉ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአስሩ ገዳይ በሽታዎች በአንደኛ ደረጃ እንዲቀመጥ አድርጎታል። በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ጨው የበዛበት ምግብ መውሰድ፣ አልኮል፣ ጫት እና ሲጋራን መውሰድ ለበሽታው አጋላጭ መንስኤዎች ናቸው።

ችግሩን ለመከላከል አጋላጭ መንስኤዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንደመፍትሔ ተቀምጠዋል። የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በማስፋት ማኅበረሰቡ የአካል እንቅስቃሴ እንዲሠራ ትኩረት ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የስፖርት ትምህርትን በሥርዓተ ትምህርት ጭምር በማካተት በትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባሕል እንዲኾን መሥራት ያስፈልጋል።

ጨው የበዛበት ምግብ አለመውሰድ፣ ውኃ መጠጣት፣ አልኮል፣ ጫት እና ሲጋራን ማቆም ይገባል። አትክልት እና ፍራፍሬ በጓሮ ጭምር በማልማት አመጋገብን ማስተካከል ያስፈልጋል፤ መንግሥትም በስፋት በማልማት ለማኅበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ በማድረግ የጤና መከላከል ላይ መሥራት ይገባል።

ይህ ኾኖ በሽታው ከተከሰተ ደግሞ በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋማት በመሔድ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል።

በዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ነገ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራ ይጀመራል።
Next article“ሚሊዬነሯ አርሶ አደር”