በተሠሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ መቻሉን የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።

70

አዲስ አበባ: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የተቀናጀ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን ተመልክተዋል።

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ወጣ ገባ የመሬት አቀማመጥ ያለው እንደ መኾኑ መጠን አፈሩ በጎርፍ ሲጠረግ እንደነበር ነዋሪዎች አንስተዋል። አካባቢው በመራቆቱም ነባር የውኃ ምንጮች መድረቃቸውን፣ የአፈር ለምነት እና ምርታማነት መቀነሱንም ተናግረዋል።

አካባቢው በከፍተኛ ደረጃ የተራቆተ በመኾኑ ለከፍተኛ የመጠጥ ውኃ ችግር ሲዳረጉ እንደነበር ነው ነዋሪዎቹ ያነሱት።

ይሁን እንጅ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተሠራው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተራቆተው አካባቢ መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ተችሏል ብለዋል። አሁን ላይ የጠፉ የውኃ ምንጮች እንደገና በመጎልበታቸው የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን እያለሙ መኾኑን ነው የጠቆሙት።

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በበጀት ዓመቱ በ498 ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤሊያስ ሸምሰዲን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችም የጠፉ ምንጮች መልሰው እንዲጎለብቱ፣ የአፈር ለምነት እና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉን ተናግረዋል፤

በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተሾመ አቡኔ በዞኑ እየተከናወነ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በአካባቢው እየተከናወነ ያለው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነትን በመጨመር እና ምርታማነትን የማሳደግ ሚናው የጎላ መኾኑንም አንስተዋል።

የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ እና መንከባከብ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው እንዳልኾነም ጠቅሰዋል። የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሕልውና ጉዳይ መኾኑን በመረዳት ሁሉም በኀላፊነት ሊሠራው እንደሚገባ ነው ኀላፊው ያሳሰቡት፡፡

በጉብኝቱ የተገኙት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ተፈጥሮን ተንከባክቦ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ በየአካባቢው የተጀመሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተቀናጁ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አበረታች እና ለሌሎች አስተማሪ እንደሚኾኑም ጠቁመዋል።

ይህን ተግባር በሁሉም አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ- ከሐረር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሐረሪ ክልል እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት ለሌሎች ክልሎች ተምሳሌት መኾን የሚችል ነው።
Next articleበአማራ ክልል ነገ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራ ይጀመራል።