
አዲስ አበባ: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢንጅነር አንዋር ሽምሰዲን በሀረሪ ክልል ሐረር ከተማ ነዋሪ ነው። በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከተሠማሩ ወጣቶች አንዱ ነው። ባለፈው ዓመት ሦስት ኾነው በማኅበር በመደራጀት 3ሺህ 500 እንቁላል ጣይ ደሮዎችን በመግዛት ሥራ መጀመራቸውን ይናገራል።
ከእነዚህም መካከል 75 በመቶው የሚኾኑት እንቁላል እንደሚጥሉ ነው የነገረን። በቀን እሰከ 3ሺህ እንቁላል እንደሚያገኙም ለአሚኮ ገልጿል። በቀን ከ4ሺህ እስከ 5ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙም ወጣት አንዋር ነግሮናል። በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በተጀመረው ሥራ አኹን ላይ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል መድረሱን ነው ወጣቱ የገለጸው።
ለ150 አባወራዎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በመንግሥት በኩል የመሥሪያ ቦታ እና ዝርያቸው የተሻሻሉ ዶሮዎችን ከማግኘት ባሻገር በጤና ባለሙያዎች ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑንም ጠቁሟል። በዚሁ ከተማ በወተት ልማት ከተሠማሩ ድርጅቶች ሌላኛው አሜን የወተት ልማት ድርጅት ይገኝበታል።

ድርጅቱ በ2001 ዓ.ም በሁለት ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞች ሥራ መጀመሩን የድርጅቱ ተወካይ ተስፋዬ አብርሐም አብራርተዋል። በሁለት ላሞች የተጀመረው የወተት ላሞች እርባታ ሥራ አኹን ላይ 115 የሚኾኑ ከብቶች መድረሱን ገልጸዋል። ከእነዚህ መካከል 35 የሚኾኑት አኹን ላይ የሚታለቡ ሲኾኑ ከእነዚህም እሰከ 350 ሊትር ወተት በቀን እንደሚያገኙ ነው የነገሩን።
ለአካባቢው ነዋሪዎች በቂ እና ጥራት ያለው የወተት ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ በተጨማሪ ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞችን እያቀረቡ እንደኾነም ጠቁመዋል። በዚህም የድርጅቱን ገቢ ማሳደግ መቻሉን ነው አቶ ተስፋዬ ያነሱት። ከላም እርባታ ባሻገር ዝርያቸው የተሻሻሉ የበግ፣ ፍየል እና ደሮም እርባታ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በሥራቸውም ከ17 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። በቂ የመሥሪያ ቦታ አለመኖር ሥራውን ከዚህ የበለጠ ለማስፋት እና የበለጠ ተጠቃሚ እንዳይኾኑ እንቅፋት መኾኑን ወጣቶቹ አንስተዋል። በመኾኑም በመንግሥት በኩል ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታ እንዲያገኙም ጠይቀዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ መንግሥት ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ብሎም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አቅዶ እየሠራ ነው ብለዋል። በሐረሪ ክልል እየተተገበረ ያለውን የሌማት ትሩፋት የጎበኙት ሚኒስትር ድኤታው የልማት ተግባሩም የሚደነቅ እና ለሌሎች ክልሎችም ተምሳሌት የሚኾን ነው ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ድኤታው ገለጻ በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ዜጎች በእቁላል፣ በወተት፣ በከብት እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በዓሣ እና በሌሎችም ዘርፎች በመሠማራት ከራሳቸው የምግብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየኾኑ ነው። በከተማ ግብርናም አትክልት እና ፍራፍሬን በማልማት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም እንደ ሀገር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ነው ሚኒስትር ድኤታው ያነሱት።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ-ከሐረር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
