“ከመጋቢት እስከ መጋቢት ባለፉት ሰባት ዓመታት”

24

ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሥርዓተ መንግሥታት ሽግግሯ ደም አፋሳሽ እንደኾነ ተደጋግሞ የሚነገርላት ኢትዮጵያ ከዘውዳዊ እስከ ዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር ልምምዷ የየዘመኑን ትውልድ ሕይዎት የቀጠፈ ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ አንዱ ወርዶ ሌላው ሲተካ “አፍርሶ መሥራት፤ አውድሞ መገንባት” እንጂ እርሾ እያተረፉ መሄድ ፈጽሞ በሀገሪቱ አልተለመደም ነበር፡፡

ከድህረ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሥልጣን ማክተም በኋላ የሀገሪቱን መንበረ ንግሥና የተቆናጠጠው ወታደራዊ መንግሥት ደርግ አጼውን ብቻ ሳይኾን ለዘመናት የተገነባውን የሥርዓት ልምምድ፣ የሀገረ መንግሥት ባሕል እና እሳቤዎች ጭምር ደብዛቸውን አጠፋቸው፡፡ ከደርግ በኋላ የመጣው የሀገረ መንግሥት ሥርዓትም ቢኾን ደርግ ያቦካው ሁሉ የማይጥመው ኾነና በርካታ በጎ ነገሮችንም አብሮ እንደ ሥርዓቱ አከሰማቸው፡፡

በጊዜው በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የበዛው የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ እና እኩልነት ጥያቄ የሥርዓት ለውጥን እንደሚያዋልድ የሚያውቁት ውስን ነበሩ፡፡ ዳሩ የሚመጣው የሥርዓት ለውጥ እንደተለመደው የብርካቶች ሕይዎት የሚገበርበት አቢዮት ወይስ ሰላማዊ ሽግግር የሚስተዋልበት የሥልጣን እርክክብ የሚለው ቀድመው ለነቁት አሳቢዎች አሳሳቢ ወቅታዊ ጉዳይ ነበር፡፡

የሥርዓቱ ሰዎችም አብዝተው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነግሩት ስለኢትዮጵያ መፈራረስ እና መበታተን ስለነበር ጭንቀቱ ተገቢም ተተንባይም ነበር ይባላል፡፡ የኾነ ኾኖ ለውጡ አይቀሬ ኾነ እና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተካሄደ። እነኾ የለውጡ መንግሥት ሀገረ መንግሥቱን ከተረከበ ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ትበታተናለች የተባለላት ኢትዮጵያም ምንም እንኳን ከፈተና ባትወጣም ብተናን አልፋ ለመጽናት የምትተጋ ሀገር ኾናለች፡፡

“ከመጋቢት እስከ መጋቢት ያለፉት ሰባት ዓመታት” በለውጡ መንግሥት በርካታ ተስፋዎች የመታየታቸውን ያክል ባይኾንም በርካታ ችግሮችም ተስተውለውበታል፡፡ ያለፉትን ሰባት ዓመታት የብልጽግና ጉዞ በሚመለከት ከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ጋር ቆይታ አድርገን ነበር፡፡

ከለውጡ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት የሥርዓት ልምምድ እና አካሄድ የግድ ለውጥን የሚያዋልድ ነበር የሚሉት አቶ ይርጋ ሲሳይ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መጥበብ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የፍትሐዊነት ችግር እና ከምንም በላይ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየደበዘዘ መምጣት የነበረውን ሥርዓት ለመቀየር ገፊ ምክንያቶች ነበሩ ይላሉ፡፡

ከኢሕአዴግ ውስጥም ከኢሕአዴግ ውጭም ያሉ ለውጥ ፈላጊዎች ቁርጠኝነት እና ትግል የፈጠረው ጥምረት የለውጡን መንግሥት ወደ ፊት እንዳመጣው ያነሳሉ አቶ ይርጋ፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ መንግሥት አሥተዳደር ታሪክ ውስጥ ደርግ “የመሬት ላራሹን” ጥያቄን እንደመለሰ ሁሉ ከለውጡ መንግሥት በፊት የነበረው የሀገረ መንግሥት ሥርዓትም “የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ” ያስተናገደበት መንገድ ከነውስንነቶቹም ቢኾን እርሾ የሚኾን ነበር ነው ያሉት፡፡

ዋልታ እረገጥ አስተሳሰብ እና ብሔር ተኮር የፖለቲካ እሳቤ ከሀገራዊ አስተሳሰብ ፍጹም መቃረናቸው እና የበላይነት መውሰዳቸው የኢሕአዴግን ዕድሜ ያሳጠሩ ኾነው ማለፋቸውንም አንስተዋል፡፡ በባለፉት ሥርዓቶች የነበሩ መልካም ልምምዶችን እንደ እርሾ በመውሰድ ችላ ተብሎ እና ተዘንግቶ የቆየውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዳር ማድረስ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ትኩረት መኾኑን አቶ ይርጋ ተናግረዋል፡፡

ዴሞክራሲ በባህሪው ልምምድ በመኾኑ ሙሉ እሳቤውን ከማስረጽ ጎን ለጎን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መገለጫ የኾኑ ተቋማትን የመገንባቱ ሂደት ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሽግግር ፍትሕ፣ ምርጫ ቦርድ እና መሰል ተቋማትንም እንደማሳያ አንስተዋል፡፡ በቀጣይም የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ በኾኑት ተቋማት ላይ ቀጣይነት ያለው የለውጥ ሥራ መሥራት፣ ነጻነት መስጠት እና እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ መሬት ማስነካት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት የነበሩ ቅራኔዎችን በመፍታት እና ልዩነቶችን በማጥበብ ኢትዮጵያዊ ኀይል ለማሠባሠብ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡ ሥልጡን እና ዘመናዊ የፖለቲካ እሳቤን ለማስፈን ያለፈውን በሚገባ የመረመረው እና መጻዒውን በውል የተረዳው ብልጽግና ፓርቲ መካከለኛውን መንገድ መርጧል ያሉት አቶ ይርጋ በፍጹም ብሔርተኝነት እና በፍጹም ኢትዮጵያዊነት መካከል ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችል ቦታ ይዟል ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያዊ አንድነት ሲባል አንድ ዓይነት ማለት ለሚመስላቸው ሁሉ ብልጽግና ከዋልታ እረገጥ እሳቤ የተላቀቀ ለመኾኑ ማሳያ እንደኾነም ያነሳሉ፡፡ ከፖለቲካ አስተሳሰብ እስከ ፖለቲካ ትልም ብልጽግና አዳዲስ እይታዎችን የተከተለ እና ዘርፈ ብዙ ለውጦችንም ያመጣ መኾኑን ማሳያዎችን በማንሳት ይጠቅሳሉ፡፡

በዲፕሎማሲው ዘርፍ ተደማጭ ሀገር ለመገንባት ብዙ እርቀቶች ተሂዶ አበረታች ውጤት እንደመጣ ያነሱት አቶ ይርጋ በግብርናው ዘርፍም ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ብሔራዊ ክብርን የማስጠበቅ ጉዳይ ትኩረት እንደተሰጠው አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የስንዴ አብዮትም አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ የሰበረ፣ ከእርዳታ እና ልመና አስተሳሰብ ያላቀቀ እና አምርቶ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ ወደ ውጭ መላክ እንደሚቻልም ያሳየ መኾኑን አንስተዋል፡፡

ብልጽግና ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩ መልካም ልምምዶችን ለማጠናከር የሚተጋውን ያክል ተገቢ ያልኾኑ ልምምዶችን ለማሻሻልም በድፍረት እና በትጋት እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ የሥራ ባሕልን ማሻሻል፣ የፖለቲካ ባሕልን መለወጥ እና ጀምሮ የመጨረስ ልምምድን ማስረጽ አኹናዊ ልምምዶች ናቸው ብለዋል፡፡

በቀጣይም ችግሮችን እየፈታ፣ መሰናክሎችን እያረመ እና ሕዝብን እያሳተፈ የኢትዮጵያን መጻዒ እጣ ፋንታ በበጎ ለመበየን ቀን ከሌሊት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሀገራዊ ክብርንና ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ በምግብ ራስን በመቻል ከተረጅነት መላቀቅ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleበሐረሪ ክልል እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት ለሌሎች ክልሎች ተምሳሌት መኾን የሚችል ነው።