
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ሥራዎች አተገባበር እና ውጤቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂዷል። በመድረኩም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የኮሙዩኒኬሽን እና የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ሃብት የሚፈጥሩ የካፒታል ፕሮጀክቶችን በመገንባት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸው ተመላክቷል።
በከተማ ሴፍቲኔት 10 ሺህ 764 የቤተሰብ ኀላፊዎች ሽግግር እንዲያደርጉ ታቅዶ 9 ሺህ 200 የሚኾኑት ሽግግር እንዳደረጉ ተገልጿል። በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ለተለያዩ የፕሮግራም ተግባራት ማስፈጸሚያ ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተብራርቷል።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ብዙ ሀብት ያላት ሀገር ኾና እያለች ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት ለመውጣት የተሠራው ሥራ በቂ አይደለም ብለዋል። በዚህ ምክንያት አሁንም ድረስ ከችግሩ አልወጣንም ነው ያሉት።
ከተረጅነት ወደ ምርትማነት ለመለወጥ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ ትልቅ አቅም መኾኑን አመላክተዋል። ሀገራዊ ክብርንና ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ በምግብ ራስን በመቻል ከተረጅነት መላቀቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የምግብ ዋስትና ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ነው ያሉት ኀላፊው ለዚህ ተግባር የሚዲያው ኀላፊነት ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብርን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተገኙ ተሞክሮዎችን ማስፋት በምግብ እህል ራስን ለመቻል አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል። በመስኖ ልማት እና በከተማ ግብርና የተመዘገቡ በምግብ ራስን የመቻል ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋውን ባታብል የምክክር መድረኩ ዓላማ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የተረጂነትን አመለካከትን ለመቀየር ሊሠሩ የሚገባዎችን ተግባራት የጋራ ለማድረግ መኾኑን አስረድተዋል። የሴፍትኔት መርኃ ግብር የብዙዎቹን ሕይወት የቀየረ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ መርሐ ግብሩ ከድህነት ሊያወጣ የሚችል በመኾኑ በአግባቡ መመራት እንዳለበት አንስተዋል። ያለንን ጸጋና እምቅ አቅም አውጥተን በመጠቀም ከድህነት መውጣት አለብን ነው ያሉት።
አባቶቻችን ነጻና ሉዓላዊት ሀገር እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም በሁለተኛው የአርበኝነት ምዕራፍ የምግብ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ በመሥራት በምግብ ራሳችን በመቻል ከተረጂነት መውጣት አለብን ብለዋል። የልማታዊ ሴፍትኔት ግቦች እንዲሳኩ የቅንጅት እና የትብብር ሥራ ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል። የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ የተረጂዎች ቁጥር እየቀነሰና በተለይ ደግሞ በልማታዊ ሴፍትኔት ታቅፈው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በዘላቂ ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የመሪዎች እና የባለሙያዎች ቅንጅታዊ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የተረጂዎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ለውጥ አምጭ ሥራዎች በሁሉም ዘርፍ ሊተገበሩ እንደሚገባ አንስተዋል። በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ የአስተሳሰብና የአመለካከት የባሕል ለውጥ በማምጣት በዘላቂነት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አመላክተዋል።
በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ቅንጅት ፈጥሮ በመሥራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ይገባል ነው ያሉት። መልማት የሚችል ሀብት እያለን የተረጂነት አስተሳሰብ መቀጠል የለብንም ያሉት ተሳታፊዎቹ መፍትሔው ችግሩን መለየትና ከችግሩ የሚያወጣ ሥራን በርብርብ ማከናወን ነው ብለዋል።
የሴፍትኔት ተመራቂዎችን በተቀመጠው መመዘኛ መሠረት እየለዩ ዘላቂ ግቦች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል። የሌማት ትሩፋት ሥራዎችንም ማጠናከር እንደሀገር የተያዘውን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
