
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ገነት በላይ ትባላለች። ገና በልጅነቷ ከትውልድ ቀዬዋ ከሰሜን ሸዋ አጣዬ ከተማን ለቃ አዲስ አበባ ከተመች። ራስ ለመቻል እና ሠርቶ ለመለወጥ ባላት ጉጉት የራሴ የምትለው ሥራ መጀመርን ከትምህርት አስቀደመች። የጀበና ቡና ለአራት ዓመታት ሠርታለች። የጽዳት ሥራም ሞካክራዋለች። ፍራሽ መሸጫ ቤትም ተቀጥራ ነበር። ሥራ ከኾነ ያልሞከርኹት የለም ትላለች።
ገነት በላይ አኹን በጨርቃ ጨርቅ ሥራ የሽመና ባለሙያ ናት። ይህንን ድርጅት በመቀላቀሌ የእለት እንጀራ ብቻ ሳይኾን ባለሙያም አድርጎኛል አለችን። በሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አመቻችነት በሽመና ሙያ ሥልጠና ወስዳ ነው ጋርመንት ተቀጠራ የጨርቃጨርቅ ሥራ የጀመረችው።
ሥራዎች ኑሮ ለመምራት ተገቢ ቢኾኑም አንዳንዴ ሴትነትን ፈታኝ የሕይወት አጋጣሚም እንዳለው ነው የገለጸችው። የቤት ኪራይ መክፈል እና ልጅ ማሳደግ ከገቢው አነስተኛነት ጋር ተደማምሮ ፈተና እንደነበረባት ትገልጻለች። ገነት ሕይወትን ለማሻሻል ከስምንት ዓመት በፊት ነው ወደ ባሕር ዳር የመጣችው። የጀበና ቡና በምትሠራ ጊዜ ስልክ የሚጠይቀው እንደሚበዛ ጠቅሳ ”ኮስተር ካልሁ ነገ ጧት አይመጡም፤ ተያይዘው ነው የሚጠፉት” በማለት ነው ሥራው ሲገኝም ያለውን ፈተና የገለጸችው።
መታለል ሊኖር ይችላል ያለችው ገነት ወጣትነት፣ ሴትነት፣ ቁንጅና እና የአቻ ግፊት ፈተናዎች እና መሸወድ ቢኖርም ከስህተት መማር ደግሞ የብልህ ሰው ባሕሪ መኾን እንዳለበት ተናግራለች። የቤት ኪራይ፣ ልጅ፣ በልቶ ማደር እስካለ ድረስ ከሕይወት እየተማሩ መቀጠል እንጂ መዘናጋት እንደማይገባም ታስተምራለች።
የምታገኘው ገቢ የሚያኖር ቢኾንም በቂ አለመኾኑን ገነት ተናግራለች። ይኹን እንጂ በሰላም ሥራ ላይ ውሎ መጠነኛ ገቢ እያገኙ ለተሻለ ሕይወት መትጋት ተመስገን የሚያስብል መኾኑን ተናግራለች። በጠዋት ሥራ አለኝ ብላ መነሳቷ እንደሚያስደስታትም ገልጻለች። በቀጣይ በሠለጠነችበት ሙያ የራሷን ድርጅት ከፍታ ለመሥራት ታስባለች። ብድር የምታገኝ ከኾነ ለሌሎችም የሥራ እድል የመፍጠርም ሕልም አላት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ መምሪያቸው ችግረኛ ሴቶችን አሰባስቦ በማደራጀት እና በማሠልጠን ሥራው ገነትም ተጠቃሚ መኾኗን ገልጸዋል። የሥራ ቁሳቁስ መግዣ እና የመነሻ ካፒታል አቅርቦት ማድረግ ወይም ሥራ ማስቀጠርም እንደተሠራ ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ ለ580 ሴቶች የሥራ እድል መፈጠሩንም አንስተዋል።
ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለ800 በችግር ተጋላጭ ሴቶች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለሥልጠና እና ለሥራ ማስጀመሪያ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል። ሴቶችን በማደራጀች፣ አቅማቸውን በማሳደግ፣ በሥነ ልቦና ግንባታ፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ ገንዘብ በማቅረብ፣ ክትትሎ እና ድጋፍ በማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ነው ወይዘሮ ሰብለ የተናገሩት።
ሴቶች ለችግር እጅ ሳይሰጡ ጥረት በማድረግ ከሕልማቸው መድረስ እና ሰው ከዋለበት መዋል እንደሚችሉ ነው ገነት የመከረችው። አኹን ላይ በየቦታው ከመባከን ድና የራሷን ድርጅት ስለመክፈት በማሰብ ላይ ናትና።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
