
አዲስ አበባ: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሐረር ክልል ሐረር ከተማ ላይ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ተመልክቷል። በሐረር ከተማ ከአሁን በፊት በቂ እና ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ባለመኖሩ ለበርካታ ችግሮች ሲዳረጉ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች አንስተዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከማስዋብ በተጨማሪ ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ተናግረዋል።እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የፈታ መኾኑንም ገልጸዋል። በሐረር ከተማ በአንደኛው እና በሁለተኛው ዙር የተከናወኑ የኮሪደር ልማቶች ከተማውን ከማስዋብ ባሻገር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መኾናቸውን የከተማዋ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኤልያስ ዮኒሳ ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ የዜጎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ እና የከተማውን ገጽታ ለማስዋብ በከተማዋ ባሉ አራቱም አቅጣጫዎች ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። የኮሪደር ልማት ሥራው ከተማዋን ለኑሮ ምቹ በማድረግ ለነዋሪዎች ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። በተለይ የሐረር ከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የሐረርን መልኮች ፍንትው አድርጎ ያሳዬ ነው ብለዋል።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ የሐረር ኮሪደር ልማት የከተማዋን እድገት ካለፈ ታሪኳ ጋር በተስማማ መልኩ እየተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል። በከተማዋ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ጽዱ እና ውብ በማድረግ የተለየ ድምቀት እንደሰጣትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ- ከሐረር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
