ፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን እና ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

220

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ 19 ሺህ 500 ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መውሰዱንና፤ ለሸማቾችና ዩኒየኖች ደግሞ ማጠናከሪያ 110 ሚሊዮን ብር ብድር መስጠቱን አስታውቋል፡፡

የቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ጣዕምያው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አማካኝነት ቫይረሱ በክልሉ በተከሰተባቸው የመጀመሪያ ጊዜያት በግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ተስተውሎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት በፍላጎትና አቅርቦት እንዲመጣጠን ቢሮው እስከ ቀበሌ የተዘረጉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ኮሚቴዎች ጋር በትኩረት እየሠራ መሆኑን ያመለከቱት፡፡

በዚህም ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም በክልሉ ያሉ 398 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች ከቢሮው ጋር ብቻ በመቀናጀት ከ150 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርት የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው መደረጉንም ኃላፊው አንስተዋል፡፡

ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኒየኖች አቅርቦት እንዲፋጠን 116 ሚሊዮን ብር እና ለገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅራት ደግሞ 180 ሚሊዮን ብር ብድር መስጠት መቻሉን አቶ ብርሃኑ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
‘‘ነጻ ገበያ ማለት ዋጋን እንደፈለጉ መጨመር አይደለም’’ ያሉት አቶ ብርሃኑ በዚህ ወቅት ያልተገባ ትርፍ በመፈለግ የዋጋ ጭማሪ እና ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙ 19 ሺህ 500 የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ከመላመድ ጋር በተያያዝ ያዝ ለቀቅ የሚሉ የኮሚቴ አሠራሮች እንዳይኖሩና በሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ ተሳትፈው የሚገኙ አካላት ላይ ርምጃ ለመውሰድ ኅብረተሰቡ አሁን የሚያደርገውን ጥቆማ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ገበያው እንዲረጋጋ በስጋት ከመጠን በላይ የምርት ክምችት እንዳያደርግ እና በማንኛውም የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርት ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም ጥቆማ በመስጠት ጤናማ የገበያ ስርዓት እንዲፈጠር ሊያግዛቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

ቢሮው በወቅታዊ የክልሉ የንግድና ገበያ ልማት ዙሪያ እና የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ የክልሉን የኮሮና ቫይረስ መቆጣጠርና መከላከል ግብረ ኃይል ፈቃድ አማካኝነት ከዞንና ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ በባሕር ዳር ምክክር እያደረገ ነው፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት በሕዝቡ ላይ የዋጋ ንረት እንዳይኖር ሕጋዊ ሥርዓቶችን የማስከበርና የማረም ሥራ እስከ ቀበሌ በተዘረጉ ግብረ ኃይሎችና ተቋማት አማካኝነት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ወዲህ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በተሳተፉ 4 ሺህ 904 ተቋማት ላይ ልዩ ልዩ ርምጃዎችን መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ 55 ነጋዴዎች ክስ ሲመሠረትባቸው 22 ነጋዴዎች ደግሞ በእሥራት መቀጣታቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች የንግድ ትስስር መፍጠራቸውን የተናገሩት ኃላፊው ለሸማቾች እና ለዩኒየኖች አቅርቦት ማሳለጫ 23 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲያገኙ ማስቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ እንግዳ ዳኘው በወቅታዊ የኮሮና ቫረስ ምክንያት የገበያ ዋጋ መቀያየሮች መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለማረም የግብይት አማራጮችንና ትስስሮችን በተቋቋሙ ግብረ ኃይሎች አማካኝነት ተግባራዊ ማድረግና የመቆጣጠር ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሕጋዊ ሥርዓቱን ባልተከተሉ 1 ሺህ 380 የንግድ ተቋማት ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰዳቸውንም አቶ እንግዳ ገልጸዋል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ለሚገኙ 19 ኅብረት ሥራ ማኅበራት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ በመደረጉም ፍላጎትና አቅርቦት እንዲጣጣም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የኮሮና ቫይረሱ በኅብረተሰቡ ላይ ኑሮ ላይ ጫና እንዳይፈጥር ፍላጎትና አቅርቦትን የሚያጣጥሙ ሸማቾችን በገንዘብ አቅም ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ ርምጃ ለመውሰድ ኅብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ጤናማ የገበያ ሥርዓት እንዲፈጠር የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የእስራኤል ሚኒስትር::
Next article“ሰው ከሚጎድለው ገንዘቡ ቀንሶ የተቸገሩትን ያግዛል፤ ገንዘብ በሁላችን ላይኖር ይችላል፤ ደም ግን በሁላችን አለ…’’ የአልማ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ