“ሠራዊታችን የተገነባበትን እሴት እና ሕዝባዊነት ተላብሳችሁ ሕዝባችሁን እና ሀገራችሁን እንድትጠብቁ አደራ ተጥሎባችኋል” ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ

42

ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለ41ኛ ዙር ያሠለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች አስመርቋል። በምረቃ መርሐ ግብሩ የተገኙት የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ተመራቂ ወታደሮች በማሠልጠኛ ትምህርት ቤቱ በተግባር እና በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን ሥልጠና ወደ ተግባር መለወጥ አለባቸው ብለዋል።

“ሠራዊታችን የተገነባበትን እሴት እና ሕዝባዊነት ተላብሳችሁ ሕዝባችሁን እና ሀገራችሁን እንድትጠብቁ አደራ ተጥሎባችኋል” ነው ያሉት። ወታደሮች በሥነ ልቦና እና በአካል ብቃት ብቁ ኾነው እንዲወጡ በትጋት ለሠሩ አሠልጣኞች እና የወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት መሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል መኮነን መንግሥቴ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቱ በየጊዜው ብቁ ወታደሮችን በማፍራት ሀገራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል። ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቱ ዛሬ ለ41ኛ ዙር በስነ ምግባር፣ በወታደራዊ ቴክኒኮች እና በአካል ብቃት ዝግጁ ያደረጋቸውን መሠረታዊ ወታደሮች አስመርቋል ነው ያሉት።

ያነጋገርናቸው ተመራቂ የሠራዊት አባላት በሥልጠና ቆይታቸው በአካልና በስነ ልቦና ብቁ የሚያደርጋቸውን ዕወቀት እንዳገኙ ገልጸዋል። በቀጣይም የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና የሕዝባቸውን ሰላም ለማረጋገጥ ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። በምረቃ መርሐ ግብሩ ተመራቂ ወታደሮች ከቀደሙ የሠራዊቱ አባላት ልምድ በመቅሰም እና መልካም ሥነ ምግባርን ተላብሰው ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክት ተላልፏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ሰላምን ማስፈን አስፈላጊ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleአፍሪካውያን ወጣቶች ለተግባራዊ ለውጥ መነሳት እንደሚገባቸው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አሳሰቡ።