
ደሴ: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች በማኅበረሰብ ላይ የተመሰረተ ማኅበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ ለሃይማኖት መሪዎች እና ለማኅበረሰብ ተወካዮች በኮምቦልቻ ከተማ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላልፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ፆታዊ ጥቃትና ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እየቀነሱ ቢኾንም በሰሜኑ ጦርነትና በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
ያለእድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት እና የመሳሰሉ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ሰላምን ማስፈን አስፈላጊ ነውም ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች ፆታዊ ጥቃት እና ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ከዚህ በፊት ለተመዘገቡ ስኬቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ነው ያሉት። በቀጣይም ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃት ሴቶችና ሕፃናት ተምረው ሀገራቸውን እና ራሳቸውን እንዳይቀይሩ የሚያደርግ ተግባር ነው ብለዋል። በመኾኑም የሃይማኖት አባቶች ፆታዊ ጥቃትና ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል። እስካሁን በተሠሩ ውጤታማ ሥራዎች የሃይማኖት መሪዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ነው ያነሱት።
ተሳታፊ የሃይማኖት መሪዎች እና አባቶች በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃትና ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ከሃይማኖት አስተምህሮዎች ውጭ የኾኑ ተግባራት ናቸው። እነዚህን ድርጊቶች ለመከላከል እንሠራለን ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሰይድ አብዱ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
