
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከፌደራል ግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የግብርና ልማቱን ያፋጥናሉ በተባሉ፦
👉 በብሔራዊ የምግብ ደኅንነት እና ጥራት ስትራቴጂ ለተቀዳሚ የግብርና ምርቶች፣
👉 ብሔራዊ የድኅረ ምርቶች አያያዝ ስትራቴጂ፣
👉 በብሔራዊ የምግብ ሥርዓት ስትራቴጂዎች እና ምግብን መሠረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር በሥርዓተ ምግብ ንቁ እና ብቁ ዜጋ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የሥርዓተ ምግብ ችግሩ ያልተቀረፈለት ዜጋ ምርታማ ሊኾን አይችልም ያሉት ምክትል ኀላፊው በምጣኔ ሃብት ልማቱ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ አለው ብለዋል።
የሥርዓተ ምግብ ጉድለት ካልተቀረፈ ውጤቱ የከፋ እንደሚኾንም ጠቅሰዋል። የምጣኔ ሃብትንም ማሳደግ እና ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማዳበር እንደሚያስቸግር ገልጸዋል።
የአማራ ክልል በሰብል እና በእንስሳት ምርቱ ለሀገሪቱ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ቢኾንም የሥነ ምግብ አጠቃቀሙ ግን ችግር እንዳለበት ነው የተናገሩት።
በፌደራል ግብርና ሚኒስቴር የግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀሚድ ጀማል (ዶ.ር) የግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የሥርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በምግብ ንጥረ ነገር ይዘቱ የበለጸገ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብ ማቅረብንም በትኩረት እየሠራበት መኾኑን ገልጸዋል።
ጥራቱ እና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ ምርት ለዜጎች ደኅንነት አስቸጋሪ እንደሚኾን ተናግረዋል። የአርሶ አደሮች ምርት ጥራት ከሌለው የልፋቱን ዋጋ ለመመለስ እንደሚቸገር ጠቅሰዋል። የምርትን ጥራት ማረጋገጥ መልሶ አርሶአደሮችን መጥቀም ነውም ብለዋል።
ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም የጥራት እና ደኅንነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደሚፈለግባቸው ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ስለ ምርት ጥራት እና ደኅንነት ተገቢ ዕውቀት እንዲኖራቸው ግብርና መዋቅሩም ኀላፊነት እንዳለበት አመላክተዋል።
የማይተላለፉ በሽታዎች የአመጋገብ ሥርዓት ችግሮች ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ ለችግሩ አንዱ ተጋላጭ አርሶ አደሮች መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ለዚህም የአመጋገብ ደኅንነትን የሚያረጋግጡ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣንም ከተደራጁት መዋቅሮች ውስጥ አንዱ ኾኖ የግብርና ምርቶችን እና ግብዓቶች ጥራት እና ደኅንነት በመከታተል እና በመቆጣጠር የብቃት ማረጋገጫ እየሰጠ መኾኑን ተናግረዋል።
ለውጪ የሚላከው ምርት አንዱ መስፈርት ጥራት እና ደኅንነት ማረጋገጥ እንደኾነም ተናግረዋል። ባለድርሻ አካላትም ይህንን ለማረጋገጥ እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
በቀጣይ ምርቶች ጥራታቸው እና ደኅንነታቸውን በየደረጃው አካል ተረጋግጦ ለገበያ እንደሚቀርቡም ገልጸዋል። ስትራቴጂውን እስከ አርሶ አደሮች ድረስ ማስተዋወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
