
ጎንደር: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ አውቶቡሶች ለመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት እንዲሰጡ መመደባቸው ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን የጎንደር ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አራት ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን በመግዛት ለከተማዋ የመንግሥት ሠራተኞች እና ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ደስተኛ መኾናቸውን የገለጹት የመንግሥት ሠራተኞቹ በሙያቸው ማኅበረሰቡን በተገቢው መንገድ ለማገልገል እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት። ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጭ መኪኖች ከመኖራቸው በፊት ታክሲዎችን በመጠበቅ ጊዜያቸው ይባክን እና በሰዓት ገብተው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ይቸገሩ እንደነበር ነው የገለጹት። አሁን ላይ ግን በከተማ አውቶብሶች ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት እያገኙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ወጭ እንደቀነሰላቸውም አንስተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አገልግሎት አቅርቦት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንዳለው ካሳ ከተማ አሥተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት ሰባት የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን ለመግዛት አቅዶ አራት መግዛቱን ገልጸዋል።
ለመንግሥት ሠራተኞች እና ለማኅበረሰቡ በቅናሽ ዋጋ ሰባት አውቶቡሶች አገልግሎት እየሠጡ እንደሚገኙ ተመላክቷል። ይህም ሠራተኞች ለማኅበረሰቡ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ለውጥ እያሳየ መኾኑን ተናግረዋል።
አውቶቡሶቹ በአንድ ጊዜ 80 ሰው የመያዝ አቅም እንዳላቸውም ተገልጿል። ከ1ሺህ 200 በላይ ለሚኾኑ መንግሥት ሠራተኞች እና ለበርካታ የከተማዋ የማኅበረሰብ አገልግሎት እየሠጡ እንደሚገኙም አብራርተዋል። በቀጣይም የኤሌክትሪክ መኪኖችን ቁጥር ለመጨመር እንደሚሠራ ገልጿል።
ተገልጋዩ ማኅበረሰብ የመኪኖችን ደኅንነት በመጠበቅ ሊጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
