የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሚጠበቅበትን የሰብዓዊ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሁሉም አካል ድጋፍ ሊያደርግለት ይገባል ተባለ።

59

ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከፊንላንድ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር በደብረ ማርቆስ ከተማ ለሚገኙ የተቋማት ኀላፊዎች እና የማኅበረሰብ ተወካዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ “ለሰብዓዊነት እንኖራለን” በሚል መሪ ቃል በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሕግ እና ውል አሥተዳደር አገልግሎት የዓለም አቀፍ ሰብዓዊነት ሕግ ከፍተኛ ባለሙያ የኾኑት አስማማው ሰጠኝ ማኅበሩ በግጭት ወቅት የሚጠበቅበትን ሰብዓዊ አገልግሎት በነጻነት መስጠት እንዲችል ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መድረክ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ አለበል ቢያድጌ ማኅበሩ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እና ሰቆቃ ለመቀነስ የተቋቋመ ማኅበር መኾኑን ገልጸዋል።

በአሁን ወቅት ካለው ግንዛቤ እና ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በአንዳንድ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ተግዳሮቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በነጻነት መስጠት እንዲችል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ማኅበሩ የሚሠራውን የሰብዓዊነት አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ እንዲሰጥ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩን ከመደገፍ አንጻርም ሁሉም አካል የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ለሰው ልጆች የሰብዓዊነት ድጋፍ በማድረግ 90 ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የድንገተኛ አደጋዎች ድጋፍ፣ የጤና አገልግሎት፣ የልማት ሥራዎች፣ የግንዛቤ ማሳደግ ተግባራት እና ራስን ለመቻል የሚረዱ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ተብሏል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መጋቢት 24 ኢትዮጵያ በታሪኳ ያልተሞከረውን አዲስ መንገድ የጀመረችበት ቀን ነው” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በብሔራዊ የምግብ ሥርዓት ስትራቴጂዎች ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።