
ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተጋረጡባትን ችግሮች በመሻገር ፈጣን ዕድገት አስመዝግባለች ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ የመጋቢት 24 ሀገራዊ ለውጥን አስመልክቶ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ፣ በከተማ እና መሠረተ ልማት እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገበውን እመርታ በአብነት ጠቅሰዋል።
መጋቢት 24 ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በማኅበራዊ መስኮች በታሪኳ ያልተሞከረውን አዲስ መንገድ የጀመረችበት ቀን ነው ሲሉ ገልጸዋል። ቀኑ ኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና ቅኝት፣ በመሃል ፖለቲካ እይታ እየተመራች ያልተሄደበትን መንገድ መጓዝ የጀመረችበት ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ ከባለፈው በጎ በጎውን በመውሰድ ለነገው ትውልድ ዛሬ ላይ ጉልህ አሻራ ለማኖር ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ የተሸጋገረችበት ቀን ነው ሲሉም ገልጸዋል። ዜጎች የሰላም አየር እንዲተነፍሱ የዘመነ፣ የሰለጠነና በሃሳብ የበላይነት የሚመራ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት የተደረገው ጥረትም ተስፋ ሰጪ ውጤት ማምጣት ጀምሯል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
