የተሻሻለው የመሬት ረቂቅ አዋጅ አርሶ አደሮች በመሬታቸው ያለሙትን ሃብት ፍትሐዊ በኾነ መልኩ እንዲጠቀሙ የሚያስችል መኾኑ ተገለጸ።

49

ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን መሬት መምሪያ የአማራ ክልል የመሬት አዋጅ 252/09ን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕግ አካላት እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አከላት በተገኙበት በደብረ ማርቆስ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን መሬት መምሪያ ኀላፊ ፋንታሁን ብርሃን እንዳሉት የተሻሻለው የመሬት ረቂቅ አዋጅ አርሶ አደሮች በይዞታ መሬታቸው ያለሙትን ሃብት ፍትሐዊ በኾነ መልኩ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው። አርሶ አደሮችን፣ አካል ጉዳተኞች እና ሴቶችን ጨምሮ አካታች በኾነ መልኩ ሁሉንም ዜጎች በመሬት ላይ ያላቸውን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በአፈጻጸሙ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት ረቂቅ አዋጁን የበለጠ ለማዳበር የሚያስችሉ ግብዓት የሚኾኑ ሃሳቦችን ለማደራጀት ባላድርሻ አካላትን ማሳተፍ አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷልም ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረው አዋጅ ውስንነቶች የነበሩበት መኾኑን ያስታወሱት መምሪያ ኀላፊው የተሻሻለው አዋጅ ግን አርሶ አደሮች በይዞታ መሬታቸው ላይ ያለሙትን ሃብት ያለገደብ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ስለመኾኑ ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ የሚወጡ አዋጆች የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት እና ጥቅም የሚያረጋግጡ መኾን አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የክልሉን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ከፌደራል መንግሥቱ የመሬት አዋጅ ጋር በተጣጣመ መልኩ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል። የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ ረቂቅ አዋጁን በአግባቡ መፈተሸ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች መሬት በተደጋጋሚ ለግጭት እና ለወንጀሎች መበራከት ምክንያት ሲኾን እንደሚስተዋል ተናግረዋል። ከመሬት ይዞታ ባለቤትነት፣ ከስጦታ እና ከውርስ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች አዋጁ መልስ የሚሰጥ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡ አርሶ አደሮች በይዞታ መሬታቸው ላይ ያሉ ሃብቶቻቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከማድረግ አንጻር አዋጁ በመልካም ጎን የሚወሰድ ስለመኾኑም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲኾን በውይይቱ የተሰጡ ግብዓቶችም ለክልል እንደሚቀርቡ ተመላክቷል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበለውጡ ጉዞ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የልማት ሂደቶች ላይ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል።
Next article“መጋቢት 24 ኢትዮጵያ በታሪኳ ያልተሞከረውን አዲስ መንገድ የጀመረችበት ቀን ነው” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)