
በሚቀጥለው እሑድ ቀን ግንቦት 9/2012 ዓ.ም 120 የእስራኤል የፓርላማ አባላት ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ፡፡ ከእነዚህ መካካል ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ቤተ እስራኤላዊት ወይዘሮ ፕኒና ታምኖ እሸቴ ይገኙበታል፡፡ ወይዘሮ ፕኒና ታምኖ የመጀመሪያዋ የገቢዎች መሥሪያ ቤት ሚንስትር በመሆን ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ። ፕኒና ታምኖ እሸቴ ጥቅምት 21/19 74 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡ በ21ኛው የእስራኤል ምክር ቤት ጥምር የፖለቲካ ድርጅቶች ሥር የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ በ19ኛውና 20ኛው የእስራኤል ምክር ቤት በየሽ ዐቲድ የፖለቲካ ድርጅት ሥር እንዳገለገሉ ግለታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ወይዘሮ ፕኒና በሙያቸው የሕግ ጠበቃ ናቸው፤ ቀደም ሲል በሬዲዮና ቴሌቪዥን መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አገልግለዋል፡፡ በተለያዩ ማኅበራትና ሕዝባዊ ድርጅቶች የቦርድ አባልና ሊቀ መንበር በመሆንም ሠርተዋል፡፡
በ2000 (እ.አ.አ) መጀመሪያ በችግር ላይ ያሉ ታዳጊ ወጣቶችን በመርዳትና የሴቶችን አቅም በመገንባት ሕዝባዊ አገልግሎት መሥጠት ጀምረዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ዘረኝነትን በመቃወም ለእኩልነት በመታገል ንቁ ተሳትፎ ያላቸው የለውጥ አቀንቃኝ ናቸው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም በዚሁ የማኅበረሰብ አንቂነታቸው ቀጥለዋል፤ በዚህም በ2016 (እ.አ.አ) የሉተር ኪንግ አርማ እና በሃኬሬን ለየዲዱት የእስራኤል አርማ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በ2012 (እ.አ.አ) የመጀመሪያዋ ትልደ ኢትዮጵያዊት የምክር ቤት አባል ሆኑ፡፡ በዚህም እስከ ምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤነት የዘለቀ ኃላፊነትን ተወጥተዋል፡፡
በ20ኛው ምክር ቤት ደግሞ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት የሚታገል ማኅበር አቋቁመዋል፡፡ ሴቶች ለደረሱባቸው ችግሮች ሥነ ልቦናዊ ማገገሚያና ማቋቋሚያ ማኅበር ሊቀ መንበር በመሆንም አገልግለዋል፡፡ ፕኒና በእስራኤል ጎልተው ከሚታዩት ከወጣትነት ብዙም ያልራቁ ሴት የምክር ቤት አባላት አንዷ ናቸው፤ የሚያተኩሩትም ለዝቅተኛ ነዋሪ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ በዋነኛነትም በእስራኤል የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማጠናከር ይታወቃሉ፡፡ የምክር ቤት አባል ሆነው ባገለገሉባቸው ጊዜያት በልጆች መብት አስጠባቂ ኮሚቴ ላይ የጎላ ተጽዕኖ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ ልጆችንና ለአደጋ የሚጋለጡ ታዳጊዎችን በተመለከተ ከፍተኛ መሻሻል እንዲታይ ስለማድረጋቸውም ነው ግለ ታሪካቸው የሚያስረዳው፡፡
በ2015 (እ.አ.አ) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ካደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ በኋላ ፕኒና ‘አዲሱ መንገድ’ የተባለውን ፕሮግራምና በሕግና ፍትሕ መሥሪያ ቤት ዘረኝነትን መታገል ያስችላል በሚል መንግሥት የወሰነውን የፌልሞር ሪፖርት የማደራጀት ኃላፊነትን በመውሰድ የጎላ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በ2014 (እ.አ.አ) የአፍሪካ ተወላጅ ተጽእኖ ፈጣሪ (MOST INFLUENTIAL PEOPLE OF AFRICAN DESCENT (MIPAD)) በተባለው ድርጅት በዓለም ላይ 100 ተጽእኖ ፈጣሪዎች ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል ወይዘሮ ፕኒና ታምኖ እሸቴ አንዷ ነበሩ፡፡
በዚህ ዓመትም የአሜሪካና እስራኤል የሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ ዋሽንግተን ዲሲ ባዘጋጀው ዓመታዊ ኮንፈረንስ የአሜሪካ ፕሬዝንዳንት፣ የኮንግረስ አባላትና በሺህ የሚቆጠሩ ታዋቂ አሜሪካውያንና እስራኤልውያን በተገኙበት ወይዘሮ ፕኒና ታምኖ እሸቴ ተጋብዘው ንግግር አድርገዋል፡፡ የምክር ቤት አባል ፕኒና ታምኖ እሸቴ በሦስት ዓመት ዕድሜያቸው ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የገቡት “ተግባረ ሙሴ” በተባለው የጉዞ ወቅት 19 84 (እ.አ.አ) ነው፡፡ ፕኒና የማስትሬት ዲግሪያቸውን በፐብሊክ ፖሊሲ በከፍተኛ ማዕረግ ከቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሕግ በቅሪያት አካዳሚት ኦኖ አግኝተዋል፡፡
መረጃውን ከእስራኤል ያደረሰን አበጀ መድኃኔ ነው፡፡