
አዲስ አበባ: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የፖለቲካ ለውጥ የተበሰረበት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያን ለማሥተዳደር ቃለ መሐላ በሕዝብ ፊት የፈጸሙበት ዕለት ነው። ይህም ዕለት ሰባተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።
ዕለቱን ለመዘከርም የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ከተማ በሰባት ዓመታት የለውጥ ጉዞ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለመዳሰስ ከተለያዩ የመንግሥት ሥራ መሪዎች እና ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ ፓርቲው በርካታ ውሥብሥብ ፈተናዎችን እየተጋፈጠ በአዲስ አበባ ከተማ አኩሪ እና ዕምርታዊ ድሎችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በለውጥ ጉዞው የፖለቲካ ሚዛንን በመጠበቅ ሁሉን ያቀፈ የፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር መሠራቱን ገልጸዋል። በሰባት ዓመታት የለውጥ ጉዞ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የልማት ሂደቶች ላይ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውንም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀው የፓናል ውይይት «ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና» በሚል መሪ መልዕክት የተዘጋጀ ሲኾን በውይይቱ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው መንግሥት በትጋት ይሠራል ተብሏል።
ዘጋቢ ፦ ራሄል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን