
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ ወራት አቅጣጫ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የባለሥልጣኑ ኀላፊ ጌትነት አማረ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በክልሉ ገበያን በማረጋጋት፣ በሰብል ግብይት፣ በግብዓት ስርጭት እንዲኹም ኢንቨስትመንት እና ቁጠባን በሚያበረታታ መልኩ ተልዕኳቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ በችግር ውስጥ ኾኖም ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገበያን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫቱ ይገኛሉ ነው ያሉት። የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሕዝቡ እያበረከቱት ያለው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ያለ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ድጋፍ የተለወጠ ኢኮኖሚ የለም ያሉት አቶ አጀበ የግብርናው ዘርፍ የበለጠ ምርታማ እንዲኾን ማኅበራቱ መልካም ሥራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል ነው ያሉት፡፡
ማኅበራቱ አግልግሎት ከመስጠት አልፈው የኢኮኖሚ ተወዳዳሪ መኾንም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ የቢዝነስ ተቋም ካልኾኑ ከውስጥ እና ከውጭ ተወዳዳሪ መኾን አያስችላቸውም ነው ያሉት፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአምራቹም ኾነ ለሸማቹ ምቹ መኾን ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ አጀበ አምራቹ ምርትን ለማሳደግ ግብዓት ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ይጠብቃል ብለዋል፡፡
ክልሉ ለዚህ ዓመት የግብርና ሥራ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ይፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም አርሶ አደሮች ከእናንተ ብዙ ይጠብቃሉ ነው ያሉት፡፡ የአርሶ አደሮች ምርት በአንዳንድ አካባቢ የገበያ እጦት ሲመግጠሙ በወረደ ዋጋ በመሸጥ እየተጎዱ ስለኾነ ማኅበራቱ ገበያ አፈላልጎ በመሸጥ አርሶ አደሮችን ማትጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ እና ማደራጃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እሸትዬ ገበያው በግብይት ረገድ ጥሩ ሥራ አከናውነናል ብለዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ከ12 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ከአርሶ አደሮች ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት የገበያ ማረጋጋት እያደረጉ ነው ብለዋል። የክዘና ተግባርም በመፈጸም ችግር ወደ አለባቸው አካባቢዎች ይጓጓዛል ነው ያሉት፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የወደራ ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበር ዋና ሥራ አሥኪያጅ አስገልለው ሙሉሸዋ አኹን ላይ 14 ሺህ ኩንታል ጤፍ ገዝተናል ብለዋል። ስንዴ ለመግዛት በሂደት ላይ በመኾናችን ገበያውን ለማረጋጋት የበኩላችን እየተወጡ እንደኾነም ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት 703 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ተዘጋጅተናል ያሉት ኀላፊው እስካሁንም 222 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!