
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የበጀት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዓ.ም የበጀት ዝግጅት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከክልል ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ጋር ውይይት አድርጓል። የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) የ2017 በጀት ዓመትን የበጀት አፈጻጸም በማየት የበጀች ሽግሽግ ለማድረግ እና የ2018 በጀት ዓመትን የበጀት ዝግጅት ሥራ ለመሥራት ውይይቱ አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።
በየተቋማቱ የበጀት አጠቃቀም ምዝገባ እና ሪፖርት በማድረግ በኩል ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰው የበጀት ሽግሽግ ለማድረግ አለመቻሉንም አንስተዋል። በሚደረገው ውይይትም የቀሪ ወራት የበጀት ሽግሽግ እንደሚደረግም ተናግረዋል። የ2018 ዓ.ም የበጀት ዝግጅት ድልድል የትኩረት መስኮችን አስቀድሞ በመጠቆም ወደ ”ፕሮግራም በጀት” የሚቀየርበትን አሠራር ትውውቅ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ቢሮው የክልል ተቋማትን የደመወዝ፣ የሥራ ማስኬጃ እና የካፒታል በጀት አጠቃቀም ሪፖርትን አቅርቧል። የሥራ ማስኬጃ በጀት አጠቃቀም አማካይም 60 በመቶ መኾኑን አመላክቷል። የካፒታል በጀት አፈጻጸምም 28 በመቶ እንደኾነ እና አፈጻጸሙም አነስተኛ መኾኑ ነው የተገለጸው። ተቋማት የበጀት አፈጻጸማቸውን አስተካክለው እና ገምግመው በ15 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉም ተጠይቋል።
በበጀት አጠቃቀም እና አሥተዳደር ላይ ያጋጠሙ ችግሮችም ተጠቁመዋል። የ2018 ዓመት በጀት ሲዘጋጅ ከተቋማት ዕቅድ የሚቀዳ እና የገቢ አፈጻጸምም ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲኾን ከማድረጉም በላይ በ25 ዓመቱ ስትራቴጅክ ዕቅድ ላይ ያተኮረ እንዲኾን እንደሚደረግ ተመላክቷል። በቀጣይም ለበጀት አሥተዳደር ትኩረት እንዲሰጥ እና ያልተጋነነ የበጀት ጥያቄ እንዲኖርም ተጠይቋል። የበጀት ፍላጎት የመኖሩን ያህል ገቢ የመሠብሠብ ፍላጎት እና አቅምንም ማሳደግ እንደሚገባ ተነስቷል።
የበጀት አጠቃቀም በአይቤክስ ተመዝግቦ ሪፖርቱ ለገንዘብ ቢሮ አለመድረሱ እንጂ የካፒታል በጀትም በሥራ ላይ መኾኑን ከተቋማት አስተያየት ተሰጥቷል። የካፒታል ፕሮጀክቶች የጥሬ ገንዘብ አለመለቀቅ እና የክፍያ መዘግየት ለካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ማነስ እንደ አንድ ምክንያት ተነስቷል። ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ምክንያት ማጥናት ችግሩን ለማቃለል እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።
የውጭ ምንዛሪ መጨመር፣ የውጭ ግዥ ሂደት እና የተመደበ የካፒታል በጀት ሥራ የማያስጀምር የሚኾንበት አጋጣሚ መኖሩም ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር እና ክፍያ ለመፈጸም ጊዜ እንደሚወስድ ተነስቷል። የፕሮግራም በጀት አመዳደብን በተመለከተም ሥራዎችን ቅደም ተከተል በመስጠት ማቀድ እንደሚገባ ተወስቷል።
በየዓመቱ በጀት እየተያዘላቸው ወደ ሥራ የማይገቡ ፕሮጀክቶች መኖራቸው ተጠቅሶ በቀጣይ በጀታቸውን በአግባቡ የማይጠቀሙ ከኾነ በጀት እንደማይመደብ ተገልጿል። የተመደበ የፖሮጀክት በጀት አነስተኛ ሲኾን የፕሮጀክቶችን ቁጥር በመቀነስ መሥራት እንደሚገባ ተመላክቷል። የበጀት አጠቃቀም በአይቤክስ ተመዝግቦ በፍጥነት ሪፖርት እንዲደረግ አቅጣጫም ተቀምጧል።
በ2018 በጀት ዓመት ለሚተገበረው ”የፕሮግራም በጀት” ሥርዓት ለባለሙያዎች እና መሪዎች በቀጣይ ሥልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ውይይቱ ቀጥሎም ከተቋማት የዕቅድ እና የበጀት አሥተዳደር ባለሙያዎች ጋር ዝርዝር ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን