በጣና ፎረም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

11

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጣና ፎረም ለአፍሪካዊ ግጭቶች መፍትሔ ስለመስጠት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2009 የወጣውን የትሪፖሊ ስምምነት ተከትሎ የተቋቋመ መድረክ ነው። መድረኩ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን ከ2011 ጀምሮ በጣና ሐይቅ ዳርቻዋ ውብ ከተማ ባሕር ዳር በየዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል።

የጣና ፎረም ዋና ዓላማ በአፍሪካ ላይ የሚስተዋሉ የጸጥታ፣ የሰላም እና የደኅንነት ሁኔታዎች ላይ በመወያየት አፍሪካ መር መፍትሔን ማፈላለግ ነው። በመድረኩ የአፍሪካ መሪዎች፣ በግጭት አፈታት ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና ምሁራን እንዲሁም መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ይሳተፉበታል።

እስካሁን 10 ፎረሞች የተካሄዱ ሲኾን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ከተካሄደው ከ9ኛው ፎረም በስተቀር ሁሉም በባሕር ዳር ከተማ ነው የተካሄዱት። ቀጣይ የሚካሄደውን 11ኛውን ፎረምም በውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ ለማካሄድ በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ (ዶ.ር) እና አምባሳደሮች ናቸው በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው ከክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ጋር የተወያዩት።

በውይይቱም ፎረሙን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የተፈጠሩ መልካም ሁኔታዎች እና ተግዳሮቶች ተነስተዋል። ባሕር ዳር እንደ ጎርጎራ ካሉ ውብ የቱሪስት ቦታዎች በቅርብ እርቀት ላይ የምትገኝ መኾኗ፣ በኮሪደር ልማት ሥራዎች የጣና ሐይቅ ውበት የበለጠ በመገለጡ እና የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱ ለፎረሙ በስኬት መካሄድ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው ተብሏል።

ይህም ወደ ቦታው የሚመጡ እንግዶች ስለአማራ ክልል ብሎም ስለኢትዮጵያ መልካም እይታ እንዲኖራቸው የሚያስችል መኾኑ በውይይቱ ተነስቷል። በቀጣይነትም ለፎረሙ ቁልፍ አጋር አካላትን የመለየት፣ የመነጋገር እና ትብብር እና ድጋፋቸውን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚከናወን ተገልጿል።

ጣና ፎረም እና ሌሎችም መሰል ሁነቶች እና ተቋማት ለኢትዮጵያ በጎ ተጽኖ ያላቸው መኾኑን መረዳት እና መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። እንዲህ ዓይነት ሁነቶች እና ተቋማትን ማንኛውም ሀገር የሚመኛቸው ናቸው፤ እኛ ደግሞ ያሉንን ዕድሎች በአግባቡ ለመጠቀም በቂ ዝግጅት ማድረግ አለብን ብለዋል ተወያዮቹ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የአንድነት ምልክት፣ የድል አድራጊነት ሐውልት”
Next articleተቋማት በጀታቸውን በወቅቱ እየተጠቀሙበት አለመኾኑን ገንዘብ ቢሮ አስታወቀ።