
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን የተፈተኑበት፣ ተፈትነው ድል ያደረጉበት፣ እንደ ወርቅ ነጥረው የወጡበት፣ እንደ ዓለት የጠነከሩበት፣ እንደ ተራራ የገዘፉበት፣ እንደ ወንዝ የረዘሙበት፣ እንደ ውቅያኖስ የጠለቁበት፣ እንደ ንብ የተባበሩበት፣ እንደ አንበሳ ድል የነሱበት፣ እንደ ነብር የታፈሩበት፣ እንደ ፀሐይ ያበሩበት፣ እንደ ጨረቃ በድቅድቅ ጨለማ መካከል ብርሃን የፈነጠቁበት፣ እንደ ጎህ የሥልጣኔ ንጋትን ያበሩበት፣ በመከራ የጸኑበት፣ በድል አድራጊነት የተሻገሩበት፣ አይቻልምን የሠበሩበት፣ የማይደፈር የሚመስለውን የደፈሩበት፣ የዘመናትን እንቆቅልሽ የፈቱበት፣ የአንድነታቸውን ምስጢር ለዓለሙ ሁሉ የገለጡበት ነው፡፡
እርሱን ለመሥራት ኢትዮጵያውያን በበረሃ ተመላልሰዋል፡፡ እርሱን ለመሥራት የሴራ ትብታቦችን ፈትተዋል፣ አያሌ ዛቻዎችን እና ማስፈራሪያዎችን ሰምተዋል፣ የበዙ ጠላቶችን ተመልክተዋል። እርሱን ለመሥራት በእሾህ እና በአሚካላ ተንከራትተዋል፡፡ እንደ ቀትር እሳት በሚናደፍ በረሃ ውስጥ ውለው አድረዋል፡፡ ላባቸውን እንደ ምንጭ ውኃ ከግንባራቸው ላይ እያፈሰሱ ጸንተዋል፡፡ ረሃብ እና ጥሙንም ችለዋል፡፡ የፈተናውን ጊዜም በጽናት አልፈዋል፡፡ በረሃውን የታገሱት፣ ነዲዱን የረሱት ለቀናት አልነበረም፣ ለሳምንታትም አይደለም፣ በወራትም ብቻም አልተወሰነም ለዓመታት ነው እንጂ፡፡
ጸንተው ሀገር አጽንተዋል፡፡ ጸንተው የገነነ ታሪክ ጽፈዋል፡፡ ጸንተው ስማቸውን በማይጠፋ ብራና ላይ አስፍረዋል፡፡ ጸንተው ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ሐውልት አቁመዋል፡፡ ጸንተው በትውልድ ሁሉ የሚመሰገኑበትን አሻራ አኑረዋል፡፡ በዘመናት መካከል የሚኮሩበትን፣ ነፍሳቸው የምትደሰትበትን ሥራ ሠርተዋል፡፡ እነርሱ የሠሩት የአንድነት መልዕክት ነው፤ የድል አድራጊነት ሐውልት ነው፡፡ እንደስሙ ታላቅ፣ እንደ ግብሩ ረቂቅ ነው ዓባይ፡፡
ዓባይ ገመድ ነው ኢትዮጵያውያን የተሣሠሩበት፣ ዓባይ እልፍኝ ነው ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚሠባሠቡበት፤ ዓባይ መሶብ ነው በአንድነት ማዕድ የተቆረሰበት፣ ዓባይ ጉርና ነው በአንድነት ወተት የተቀዳበት፣ ዓባይ ጽዋ ነው በአንድነት ወይን የተጠጣበት፣ ዓባይ ሕብስት ነው ትውልድ ሁሉ ተመግቦ የሚጠግብበት፣ ዓባይ በጠማ ጊዜ የተገኘ ፍሩንዱስ ነው ትውልድ ሁሉ ከጥሙ የሚረካበት፤ ዓባይ ብራና ነው የማይጠፋ የታሪክ መዝገብ የሠፈረበት፣ ዓባይ ብዕር ነው የማያልፍ ታሪክ የተጻፈበት፣ ዓባይ መንገድ ነው ኢትዮጵያውያን በአንድነት የተጓዙበት፣ ዓባይ ቅኔ ነው ኢትዮጵያውያን የሚቀኙት፣ ዓባይ ጥበብ ነው ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበት፣ ዓባይ ሸማ ነው ኢትዮጵያውያን ፈትለው፣ ዘሃውን አዝግተው አሳምረው የሠሩት፣ ዓባይ ጥላ ነው ኢትዮጵያውያን የሚያርፉበት፣ ዓባይ ጀምበር ነው ኢትዮጵያውያን ያበሩበት፣ ዓባይ ምልክት ነው ኢትዮጵያውያን የሚለዩበት፣ በዓለሙ ሁሉ የሚታወቁበት፣ ዓባይ ምስጢር ነው ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚፈቱት፣ ዓባይ ቤተ መዝክር ነው ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚጎበኙበት፡፡
ዓባይ ረቂቅ ነው ጠላቶች የማይመረምሩት፣ ዓባይ ተስፋ ነው በአይቻልም ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ተስፋ የሚያደርጉት፤ ዓባይ አብነት ነው ትውልዶች ሁሉ ይቻላልን የሚማሩበት፤ ዓባይ ትናንት ነው የትናንት ታሪክ የሚነገርበት፣ ዓባይ ዛሬ ነው የዛሬ ታሪክ የሚጻፍበት፣ ዓባይ ነገ ነው ተስፋ እና ራዕይ የሚቀመጥበት፣ ዓባይ መስታውት ነው ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ በኅብረት የሚታዩበት፡፡ ዓባይ ኅብረ ቀለም ነው ኢትዮጵያውያን ያጌጡበት፡፡ የሚያጌጡበት።
ኢትዮጵያ በዓባይ ድልን ተቀዳጅታለች። የዘመናት አሸናፊነቷን አጽንታበታለች። አይደፈሬነቷን አሳይታበታለች። ለማንም በርከክ እንደማትል አረጋግጣበታለች። ዓባይ የማይናወጥ ቤት ነው ኢትዮጵያውያን በአንድነት የገነቡት። ዓባይ ትምህርት ቤት ነው ዕልፍ አዕላፍ ዕውቀት የሚገበዩበት፣ ዓባይ ግድብ ብቻ አይደለም ውኃ የሚጠራቀምበት፣ ዓባይ ግድብ ብቻ አይደለም ዓሣ የሚረባበት፣ ዓባይ ግድብ ብቻ አይደለም ኀይል የሚመነጭበት። ዓባይ ከግድብነት የተሻገረ፣ ትናንትን ከዛሬ እና ከነገ ጋር ያስተሳሰረ፣ ኢትዮጵያዊነትን በጽኑ መሠረት ላይ ያኖረ ሕያው ቅርስ ነው እንጂ።
“ውሾች ይጮሃሉ ግመሎች ይጓዛሉ” የሚለው ብሒል የተፈጸውም በዓባይ ግድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብን ለመገደብ ካሰበችበት ጊዜ እስካሁን ድረስ አልፍ አዕላፍ ውሾች ከውስጥም ከውጭም ጮኸዋል፡፡ ብትነኩት ወዮላችሁ የሚሉ ድምጾች ተሰምተዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን የሚቆርጡ ሰይፎች ተስለዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን የሚወጉ ጦሮች ተሹለዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን የሚገረስሱ መሣሪያዎች ተሠባሥበዋል። ዳሩ ሁሉም ከኢትዮጵያውያን አንድነት እና ኅብረት፣ ከኢትዮጵያውያን ጀግንነት እና አይደፈሬነት በታች ነበሩ።
ውሾች ጮኸዋል። ግመሎች ግን ከመንገዳቸው ሳይቆሙ ተጉዘዋል፡፡ በረሃውን አቋርጠው ካሰቡት ስፍራ ደርሰዋል፡፡ ዛሬም በጉዟቸው ቀጥለዋል፡፡ የወጠኑትን ለመቋጨት የመጨረሻው ዙር ላይ ደርሰዋል። በኅብረታቸው የመጨረሻውን ሳቅ ለመሳቅ ተቃርበዋል። ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን በዓድዋ ላይ በጦርነት፣ በዓባይ ደግሞ በልማት በመከራ ጸንቶ ድል መንሳትን አስተምረዋል፡፡ አርዓያነታቸውን አስጠብቀዋል። ከጥንት የጥቁሮች ምልክት፣ የነጻነት እናት የነበረች ኢትዮጵያ ዛሬም በአሸናፊነት ምልክትነቷ፣ በጠነከረ አንድነቷ ዳግም ታይታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መጋቢት 11 2017 ዓ.ም በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉባኤ በሰጡት ማብራሪያ ሕዳሴ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ነው፤ አንድ ብር ከውጭ ያልተገኘበት ነው ብለው ነበር። ብዙ ፈተና አይተንበታል፤ በሕዳሴ ግድብ የውጩ ጫና የበረከተ ነበር፤ ነገር ግን መከራዎች ታልፈው በሚቀጥሉት ወራት እናስመርቃለን፣ ሕዳሴ ከወራት በኋላ የተጻፈ የሚነበብ ታሪክ ይኾናል ነበር ያሉት፡፡
“ሕዳሴ የአፍሪካ ኩራት ነው፤ ሕዳሴ ለመላው አፍሪካ መቻልን ያሳየንበት ነው፤ ሕዳሴ ስህተትን ያረምንበት ነው፤ አፍሪካውያን ብድር ቢከለከሉ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ቢደረግባቸው፣ የራሳቸውን ሃብት በገዛ ዜጎቻቸው ማልማት እና መቀየር እንደሚችሉ በተግባር የሚያስተምር ሥራ ነው ” ብለዋል።
ሕዳሴ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ የበራበት ድንቅ ሥራ ነው ። ያየው ሁሉ የሚደመምበት ረቂቅ አሻራ ነው።
በቅርቡ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ.ር) ሕዳሴ ግድብ ለዚህ ዘመን ትውልድ የተሰጠ ዕድል፣ ሁለተኛው ዓድዋ ነው ይላሉ፡፡ አንድም ብድር፣ አንድም እርዳታ ሳናገኝ፣ በበርካታ ዲምሎማሲያዊ ጫና ሥር ኾነን ለኢትዮጵያ ሁለተኛው ዓድዋ ለማጠናቀቅ ተቃርበናል ነው ያሉት።
ግድቡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ እና የፍላጎት ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተው በጋራ ያሳኩት፣ በጋራ የገነቡት ነው ይላሉ፡፡ ይህ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብሥራት፣ ትልቅም ትምህርት ነው የሚሉት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ሕዳሴ በጋራ ስንቆም ታምዕር መሥራት እንደምንችል፣ ስንለያይ ደግሞ ችግር ውስጥ እንደምንገባ ቋሚ ማሳያ ነው፣ አፍሪካውያን ከወሰን፣ ከቆረጥን ማድረግ እንደምንችል ታላላቅ ጉዳዮችን ማሳካት እንደምንችል፣ ማሳያ ነው ይሉታል።
ሕዳሴ እውነትም የኢትዮጵያውያን የላብ እና የደም ውጤት ነው። የተስፋ እና የማደግ አብነት ነው። የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተፈተነበት፣ ተፈትኖም ድል የተነሳበት ነው ይላሉ። ሕዳሴ ሲታሰብም ኾነ ሢሠራ ትልቅ ፈተና ገጥሟል፣ ሕዳሴ በተጀመረ ጊዜ ከአፍጋኒስታን እና ከኢራቅ ጦርነት ባላነሰ በሚዲያዎች ሽፋን አግኝቷል፣ ያም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጫና የሚያሳድር የሚዲያ ሽፋን ነበር ነው የሚሉት።
ግብጾች ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ምንም እንዳትሠራ ይፈልጉ ነበር፣ ለዚያም የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። መንግሥታቸውም ኾነ ሕዝቡ ኢትዮጵያ ዓባይን እንዳትነካ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን አልተሳካላቸውም። ዓባይ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሠሩት፣ በአንድነት ጀምሮ በአንድነት ለመፈጸም ጫፍ ያደረሱት ነው ይላሉ። እንደ ዓድዋ ሁሉ የተባበሩትበት፣ ፈተናውንም አሸንፈው ድል የነሱበት ነው ይሉታል።
አሁን ውኃ እና አፈር ሲገብሩ መኖር ቀርቷል። ሕዳሴ ዕውን ኾኗልና። ሕዳሴን ከዚህ በኋላ ማንም መንካት አይቻለውም። ኢትዮጵያውያን አንድ ሲኾኑ እና ሲተባበሩ ዓለምን የሚያስደንቅ ሥራ ይሠራሉ። ሠርተዋልም። ሕዳሴ ኢትዮጵያውያን አይስማሙም፣ አይግባቡም፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ የተለያዩ ናቸው፣ በውስጣቸው አንድነት የለም የሚሉንን ያሳፈረ እና ሃሳባቸውን ውድቅ ያደረገ ነው ይሉታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ያረጋገጠበት፣ ሁሉም ያዋጣበት ነው።
ኢትዮጵያውያን አንድ ከኾኑ ማንም እንደማያሸንፋቸው፣ ማንም ወደኋላ እንደማይመልሳቸው ግልጽ ትምህርት የሰጠ ነው ይሉታል ፕሮፌሰሩ። እነኾ ሕዳሴ የአንድነት ምልክት፣ የድል አድራጊነት ሐውልት፣ የኢትዮጵያ የጽናት አብነት ኾኖ ይኖራል። ትውልድን ከትውልድ ያስተሳስራል። ፍቅርን እያበሠረ በዘመናት መካከል ይዘልቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!