አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ መታደጉን ገለጹ።

12

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመራሮቸና አባላት “ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ መልእክት የለውጡን 7ኛ ዓመት አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚህ ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ መጋቢት 24 የተጀመረው ለውጥ በአይነቱ የተለየና የተሳካ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ለውጡ ሕዝባዊ፣ ሕገ-መንግሥታዊና ድርጅታዊ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የለውጥ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ለለውጡ ስኬታማነት የተወጡት ሚና በታሪክ የሚወደስ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ማስገኘቱን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ የታዳገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በለውጡ በኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲ መስኮች የተገኙ ውጤቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የጨመሩ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ለውጡን ማስቀጠልና የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁሉም ኀላፊነት መሆኑን የተናገሩት አፈ ጉባዔው የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን በሠላማዊ ንግግርና ውይይት ብቻ መፍታት የስልጡንነት መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ለውጡ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት ያጠናከረ እንዲሁም የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና የፖለቲካ ተሳትፎ ያረጋገጠ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በዴሞክራሲ ሥርዓትና በተቋማት ግንባታ የመጣው ለውጥ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ማሳደጉን አስረድተዋል፡፡

ሕዝቡ ለውጡ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
Next article“የአንድነት ምልክት፣ የድል አድራጊነት ሐውልት”