በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

12

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ እና በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በማስከተል ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። በክልሉ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ መከሰቱን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎች እና የጤና ሁኔታዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ሲስተር ሰፊ ደርብ እንደገለጹት ወረርሽኙ ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ በየቀኑ የሚደርሰው የበሽተኛ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በተለይ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ በቀን ውስጥ በርካታ ሰዎች በበሽታው እየተጠቁ ነው ብለዋል።

የኮሌራ የተበከለ ውኃ እና ምግብን በመጠቀም የሚከሰት ሲኾን ሰዎች በብዛት በሚሠባሠቡባቸው ቦታዎች በተለይም ንጹህ የመጠጥ ውኃ እና ንጹህ የመጸዳጃ ቦታ በሌለበት አካባቢ በቀላሉ ይተላለፋል ነው ያሉት።

በሽታውን ለመከላከል ኅብረተሰቡ የግል እና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ፣ ንጹህ ውኃን መጠቀም፣ ምግብን አብስሎ መመገብ እና ምግብ ከማብሰል በፊት፣ ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ እና ከበሽተኛ ጋር ንክኪ ከተደረገ በኋላ እጅን በሳሙና መታጠብ አስፈላጊ እንደኾነም አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ውኃን በኬሚካል አክሞ እና አፍልቶ መጠቀም እንዲሁም የበሽታው ምልክቶች ከታዩ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል።

በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት ከሌሉ ወይም ለሚመለከታቸው የጤና ባለሙያዎች ማድረስ ካልተቻለ ኅብረተሰቡ የክልሉን ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነጻ የስልክ መስመር 6981 በመጠቀም መረጃ መስጠት እንደሚችልም ሲስተር ሰፊ ደርብ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ችግሩ ምንም ይሁን ምን መፍቻ ቁልፍ ያለው መመካከር ላይ ነው” ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር)
Next articleአፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ መታደጉን ገለጹ።