
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ለሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ የቅድመ አጀንዳ ማሰባሰብ የግንዛቤ መፍጠሪያ የፓናል ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በፓናል ውይይቱ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ ኮሚሽነሮች፣ የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሚዲያ አካላት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) ለሀገራዊ መጻዒ ዕድል ሰላም መሠረታዊ ነገር መኾኑን አመላክተዋል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንዳለ ሰው በሀገራዊ ምክክር ማመን መሠረታዊ ነገር መኾኑን አንስተዋል። አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ በዘላቂነት ለመውጣት ምክክር ማድረግ ብቸኛ ፍቱን መድኃኒት ነው ብለዋል። እንደ ሕዝብ ምክክርን ባሕል ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
በዚህ ዘመን ላይ ኾነን በተኮራረፍን ቁጥር ጠመንጃ መፍትሔ መኾን የለበትም ብለዋል። አሁን ካለንበት ሀገራዊ የጸጥታ ችግር ለመውጣት ልሂቃን ትልቅ ድረሻ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። በተለይም ትልቁ የልሂቃን ሚና ለሕዝብ መልካም ተስፋ ማሳየት መኾንን ነው ያነሱት።
” የምመክረው ችግሩ ምንም ይሁን ምን መፍቻ ቁልፉ ያለው መመካከር ላይ መኾን እንዳለበት ነው” ብለዋል። በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት ከመጭው ቅዳሜ ጀምሮ እንደሚካሄድም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!