
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገው 3 ሺህ 707 የላብራቶሪ ምርመራ 15 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 287 ደርሷል፡፡ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ አራት ተጨማሪ ሰዎች ማገገማቸውንም ጤና ሚኒስቴር ገልጧል፡፡
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወንዶች ናቸው፡፡ እድሜያቸው ደግሞ ከ17 እስከ 38 ነው፡፡ ከእነዚህ ወስጥ ስምንት ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ ሁለት ሰዎች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ለይቶ ማቆያ፣ አንድ ሰው ከአፋር ክልል ሰመራ ለይቶ ማቆያ፣ አንድ ሰው ከአማራ ክልል መተማ ለይቶ ማቆያ፣ ሶስት ሰዎች ደግሞ ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ናቸው፡፡
እንደ ጤና ሚኒስቴር መግለጫ ሰባቱ የውጭ ሀገራት የጉዞ ታሪክ አላቸው፤ አንድ ሰው የውጭ ሀገራት የጉዞ ታሪክም ሆነ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የለውም፡፡ ሌሎች ሰባት ሰዎች ደግሞ በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር ንክኪ ነበራቸው፡፡
በኢትዮጵ የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ለ48 ሺህ 985 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ 287 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ጃፓናውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታዎሳል፡፡
በአጠቃላይ 112 ሰዎች አገግመዋል፤ አምስት ደግሞ ህይዎታቸውን አጥተዋል፡፡
አሁን ላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው 168 ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡ ዛሬ በጽኑ ህሙማን ማከሚያ ውስጥ የገባ ታማሚ አለመኖሩንም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡