ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከንጋት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር 25 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ ዱቄት ድጋፍ አደረገ።

21

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዳሽን ቢራ ፋብሪካ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አሥኪያጅ አብርሃም ዘሪሁን እንደገለጹት ፋብሪካው ባለፉት 25 ዓመታት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። የትምህርት ቤት ግንባታ፣ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የደረሱ ጉዳቶችን መልሶ ማቋቋም እና ጤና ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎች ናቸው።

አኹን ላይ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለተከሰተው የምግብ እጥረት ከንጋት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር 25 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል። ከዚህ በፊትም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ የዕለት ደራሽ የምግብ ዱቄት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በ225 ሚሊዮን ብር በጎንደር አዳሪ ትምህርት ቤት ለመገንባት እየተሠራ ይገኛል። በቀጣይም በክልሉ የማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ምክትል ኮሚሽነር ሰርክ አዲስ አታሌ እንዳሉት በክልሉ ውስጥ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ ከአጋጠማቸው አካባቢዎች ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንዱ ነው።

አካባቢው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በድርቅ፣ በጎርፍ እና በበረዶ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል። በዚህ ዓመት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 240 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሯ ዳሽን ፋብሪካ ያደረገው ድጋፍ ችግሩን ለመቅረፍ አቅም ይኾናል ብለዋል።

ፋብሪካው 28 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የምግብ ዱቄት ድጋፍ ማድረጉን ነው የገለጹት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሰዎች ያለምንም ማመንታት ለሀገራቸው የሚበጀውን ሀሳብ ማዋጣት አለባቸው” ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
Next articleየሰቆጣ ቃልኪዳን የማሥፋፋት ምዕራፍ ትግበራ ሥራ በሁሉም ክልሎች እየተተገበረ መኾኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡