
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግድቡ ሲጀመር “ኢትዮጵያ ከኛ ችሮታ ውጭ በራሷ አቅም መገንባት አትችልም” ያሉ በርካቶች ነበሩ። ፕሮጀክቱ ለአብዛኛዎቹ የዓለም ሀገራት ሕልም ቢመስልም ኢትዮጵያውንን ደግሞ ከዳር እስከ ዳር ያነቃነቀ፣ ሀገራዊ አንድነትን ያሳየ ኾኖ ብቅ አለ።
የበርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት የኾነው የአማራ ክልል ሕዝብ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ይፋ ከኾነበት ጊዜ ጀምሮ ከዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል እስከ ባለጸጋው በጉልበት እና በገንዘብ አሻራውን እያስቀመጠ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪው ጡረተኛው አቶ ፋንታ መስተሳህል አንዱ ናቸው። አቶ ፋንታ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተቀጥረው በተለያዩ አካባቢዎች አገልግለዋል።
የዓባይ ወንዝ ለእናት ሀገሩ ባዕዳ ለጎረቤቶቹ ደግሞ ባለሟል፣ የእድገታቸው መነሻ መኾኑ ያስቆጫቸው ነበር። መጋቢት 24/ 2003 ዓ.ም የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲበሰር በታሪክ አጋጣሚ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ግንባር ቀደም ኾኑ። ለ15 ዓመታት ያህልም ከጡረታ ገቢያቸው በየወሩ 1 ሺህ ብር በመቆጠብ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሻራቸውን አሳረፉ። እስካሁን ድረስ 168 ሺህ ብር የሚገመት ቦንድ ገዝተዋል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በርካታ ችግሮችን አልፎ ለፍጻሜ በመቃረቡ የተለየ ስሜት እንደተሰማቸው ለአሚኮ ተናግረዋል። ሃምሳ አለቃ መንበሩ አንዱዓለም ደግሞ የባሕር ዳር ነዋሪ ናቸው። በ1975 ዓ.ም የኢትዮጵያን ሠራዊት በመቀላቀል ለሀገራቸው አገልግለዋል። አኹን ላይ ደግሞ በጥበቃ ሥራ ላይ እያገለገሉ ይገኛሉ። ከሚያገኙት ገቢ ለዓባይ ግድብ አበርክተዋል።
ከራሳቸው አልፎ አምስት ቤተሰቦቻቸው ጭምር ለግድብ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ አድርገዋል። በቅርቡም ለልጃቸው አንደኛ ዓመት ልደት የሕዳሴውን ግድብ ቦንድ ነበር በሥጦታ ያበረከቱት። በቀጣይም ለኢትዮጵያን እድገት እውን ለሚኾን ልማት ሁሉ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። የአኹኑ ትውልድም ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ለሀገሩ በጋራ ሊቆም እንደሚገባ መክረዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአማራ ክልል ማሥተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይነህ ጌጡ እንዳሉት ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በክልሉ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ድርጅቶች እና ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ መንገዶች ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተሰብስቧል።
ከዚህ ውስጥ፦
➽. 556 ነጥብ 34 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት ሠራተኛው፣
➽. 107 ነጥብ 21 ሚሊዮን ብር ከባለሀብቱ እና ከንግዱ ማኅበረሰብ፣
➽. 241 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ከአርሶ አደሮች፣
➽. 368 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ከድርጅቶች እና ተቋማት እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣
➽. 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ደግሞ በልገሳ የተገኘ ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች ውስጥም ኾኖ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከማበርከት ያላገደው ክልል እንደኾነ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ብቻ 68 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል። ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የክልሉ ሕዝብ በአፈር እና ጥበቃ ሥራ ከፍተኛ የጉልበት አስተዋጽኦ አበርክቷል። ባለፉት 14 ዓመታት 38 ቢሊዮን ብር የሚኾን የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው ኀላፊው የገልጹት።
ኢትዮጵያውያን ያበረከቱት የጉልበት እና የገንዘብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ፍሬ ሊያፈራ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመኾኑ መላው ሕዝብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። በክልሉም ኾነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚገነቡ ታላላቅ የልማት ሥራዎች የሚደረገው ተሳትፎም ባሕል ሊኾን ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን