
ጎንደር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ14 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መኾኑን አስታውቋል።
አርሶ አደር ታከለ ወሌ እና አርሶ አደር ሃጎስ ያለው የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንደደረሰ ተናግረዋል። የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ግን በሚፈለገው ልክ ግዥ ፈጽመው የአፈር ማዳበሪያን ለመጠቀም እንደተቸገሩም ገልጸዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት ለመጠቀም ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውንም አንስተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እና የሰብል ብዜት ባለሙያ ገብሬ ደሳለኝ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
እንደ ጎንደር ከተማ 21 ሺህ 980 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ባለሙያው በአሁኑ ወቅት ከ14 ሺህ 558 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መኾኑን አስታውቀዋል።
የአፈር ማዳበሪያ የስርጭት ሂደቱ አርሶ አደሮች ባላቸው መሬት ልክ ታሳቢ ተደርጎ እየተከፋፈለ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ማሳየቱን ያስረዱት አቶ ገብሬ የዋጋ ጭማሪው የዓለም አቀፍ ግብይትን ተከትሎ የተከሰተ መኾኑን ገልጸዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንደ አማራጭ መጠቀም ተገቢ መኾኑን አመላክተዋል።
በሚጠበቀው ልክ የአፈር ማዳበሪያ ወቅቱን ጠብቆ እንዲደርስ ለማስቻል እንደሚሠራም አስታውቋል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን