አባይን በዜማ

48

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ድሮም ከጥንተ ፍጥረቱ የጥበብ ምንጭ ነው። ከባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን እስከ እረኛ ባለዋሽንቶች ስለዓባይ፣ ዓባይም ለእነሱ የጥበብ ማፍለቂያ፣ የስሜታቸው መግለጫ ነው። ከአረጋኸኝ ወራሽ “ዓባይ ያበቀላት” እስከ አብርሃም በላይነህ “እቴ ዓባይ” ድረስ የፍቅር መጥለቂያ ነው ዓባይ። ብዙዎች በፍቅር የተዋደዱባቸው፣ በትዳር የተጋመዱባቸው ዜማዎች መፍለቂያ ነው ዓባይ።

ወዲህ ደግሞ ዓባይ መብራት፣ ልማት፣ ኩራት መኾን ጀምሯል። የጋዜጠኛው የሀሳብ ማጠንጠኛም ይህ ነው። ባለቅኔዋ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዓባይ ያለውን ግርማ ሞገስ ከእግር እስከ ራሱ ውብ አድርጋ ገልጻዋለች። ዓባይ ውበቱ የማያረጅ፣ ቁንጅናው የማያልቅ መኾኑን በስንኞቿ አሳይታለች።

እድሜ ልኩን ቢጓዝ እሱም እማይሰለቸው፣ ተፈጥሮም የማያነጥፈው የገነት ውኃ ስለመኾኑ ጂጂ ተቀኝታበታለች። ግርማ ሞገሱ የሚያስፈራ፣ የኢትዮጵያ የሀገር ልብስ ኾኖ ሳለ ምነው ዓባይ የበርሃ ሲሳይ ኾነ? ስትልም ትጠይቃለች። ይሄ ጥያቄ የመላው ኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ ነበር። አሉ አይደል አንዳንድ ቁጭቶች በእንጉርጉሮ የማይወጡ፣ በእንባ የማይፈስሱ? የውስጥ እሳት ኾነው ሁሌም የሚፋጁ? ዓባይ እንዲያ ነበር መላ ኢትዮጵያውያንን በቁጭት ሲያንገበግባቸው የኖረ።

አሁን የባለቅኔዋ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ጥያቄ ተመልሷል። ዓባይ በቤቱ ውስጥ አድሯል። በሕዳሴው መንገድ መገማሸር ጀምሯል። የሙዚቃ ምቱም ተቀይሯል።

ሕጻናት በሕብረ ዜማቸው:-
“እንጉርጉሮ ይብቃ ይገባል ውዳሴ፣
ጉዞውን ጀምሯል ዓባይ በሕዳሴ” ማለት ጀምረዋል።
አሁን ላይ ዓባይ የኔ ነው የሚል ትውልድ ተፈጥሯል።
“ዓባይ ቅኔ ነው የእናት ኢትዮጵያ የአብራኳ ክፋይ፣
የሚፍለቀለቅ ከአምባዎቿ ላይ፣
ውኃ ብቻ አይደለም ፈሳሽ ወራጅ ውኃ፣
የሀገር ምሰሶ የትውልድ አምሐ” እያለ የሚቀኝ ትውልድ መጥቷል። በተባበረ ክንድ ዓባይን ገድቦ ወደ ማገባደጃው ተቃርቧል።

ያኔ ጂጂ ዓባይ ማደሪያ ሳይኖረው ግንድ ይዞ ሲዞር በነበረበት ወቅት እንዲህ ብላው ነበር:-
“ዓባይ የወንዝ ውኃ አትኾን እንደሰው
ተራብን ተጠማን ተቸገርን ብለው
አንተን ወራጅ ውኃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን አስቀምጠሀል ከግብፆች ከተማ?
ዓባይ ወንዛወንዙ ብዙ ነው መዘዙ” ስትል በቋጠረቻቸው ስንኞች ዓባይን ለመገደብ እና ለመጠቀም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ምን ያህል ስጋት እንደነበር አመስጥራዋለች።

አሁን ይሄ ትርክት ተቀይሯል። መፍራት እና መሸበር ቀርቷል። የቴዲ አፍሮ “ደሞ በዓባይ ድርድር” በሚል ያዜመው ዜማ የዚህ ማሳያ ነው፡- “ደሞ በዓባይ ድርድር ደሞ በዓባይ
ማን ዝም ይላል ኾኖ ዜጋ፣
ዓባይ ለጋሱ ግብጽን አርሶ፣
ሀገሬን ባለ ልይ ተመልሶ፣
ብሎ አሻፈረኝ ለሳበ ቃታ፣
እኔን አያርገኝ የነካኝ ለታ” ሲል በዓባይ ጉዳይ የኢትዮጵያውያንን ልበ ሙሉነት አንጸባርቋል።
ዛሬ ላይ ዓባይም ዳገቱን ወጥቶ ተሞሽሯል። ኢትዮጵያውያንም “ጉሮ ወሸባዬ” ሊጨፍሩለት ጥቂት ወራት ብቻ ቀርተዋል።

በደመወዝ የቆዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሀገራዊ ለውጡ የመጣበትን እና የሕዳሴ ግድብ የተጀመረበትን ቀን አስመልክቶ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው።
Next articleበጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ14 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው።