ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አዲስ እና ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ ኾኗል።

42

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይነህ ጌጡ ለአሚኮ እንደተናገሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ኤሌክትሪክ ከማመንጨት ጎን ለጎንም ለዘርፈ ብዙ የቱሪዝም አገልግሎት የተመቸ ኾኖ እየተገነባ ነው ብለዋል፡፡ ግድቡ አዲስ እና ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻም ኾኗል።

በግድቡ በርካታ ደሴቶች ተፈጥረዋል ያሉት ኀላፊው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝውን በማዝናናት የገቢ ማስገኛ ይኾናሉ ነው ያሉት፡፡ አቶ ዓባይነህ በግድቡ ግንባታ በርካታ ማኅበረሰብ ተሳትፎበታል ይላሉ፡፡ በመኾኑም በአካባቢው እጅግ ዘመናዊ ከተማ ከመገንባት በተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይዞ እየመጣ ነው ብለዋል፡፡

በግድቡ ሰፊ የዓሳ ምርት በመኖሩ አሁን ላይ ዓሳ ለሚያሰግሩ እና ተደራጅተው ለሚሠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በቀንም ከ14 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የዓሣ ምርት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አምርተው ለገበያ እያቀረቡ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

የሕዳሴው ግድብ ብዙ ጠቀሜታዎችን ይዞ እየመጣ ነው ያሉት አቶ ዓባይነህ የአካባቢውን የአየር ንብረትም በአዎንታ ይቀይራል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅም የአማራ ክልል ሕዝብ በውሰጡ ያለበትን ችግር ተቋቁሞ ከፍተኛ ድጋፍ ስለማድረጉም አስገንዝበዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ እስካሁንም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ ጫፍ የደረሰውን ግንባታ ለማጠናቀቅም ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ ይሠራል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ሽግግር ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መኾኗን በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ገለጹ።
Next article“ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት እየራቀ፣ ነገ እየቀረበ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ