
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2012 ዓ.ም (አብመድ) ቁመቱ 828 ሜትር ይረዝማል፤ የዓለማችን ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ነው። በዱባይ መሬት ላይ የቆመው ይህ ሕንፃ ውበቱ ውብ ነው። አምናና ታች አምና በረመዳን ወቅት በገበያተኛ ተሞልቶ ጠጠር መጣያ ቦታ አይገኝለትም ነበር፤ ዘንድሮ ግን ወረርሽኙ ወደ ዱባይ ስለገባ በአጠገቡ ዝር የሚል የለም፤ ሰው አልባ ሆኗል።
‘‘ይህንን የመሰለ ሕንጻ ሰማይን ሊነካ ቆሞ ለምን አፉን ከፍቶ ይቀመጣል?’’ ያሉ የሀገሬው ሰዎች ታዲያ መላ ዘይደውለታል። በሀገረ ዱባይ ወረርሽኙ ሲገባ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራ አጥተዋል። በተለይ የረመዳን ፆም ሲጀምር ፆመኞቹ ፆመው ውለው ፆማቸውን ያድራሉ፤ እህልና ውኃም ይቸገራሉ።
ልቦናቸው በጎ ያሰበው የሀገሬው ደግ ሰዎች ‘‘ሰማይ ጠቀሱ ፎቅ ቆሞ ከሚቀር፤ ፆመኞቹም ረሀብ ከሚያንገላታቸው ስንቅ ማከማቻ ቢሆንስ?’’ አሉና ዘመቻ ጀመሩ። ለዕርዳታ ፈላጊዎቹ ያለው ብቻ እንዳይሰጥ የሚሰበሰበውን የዕርዳታ ስንቅ ልክ አበጁለት።
አንድ የዱባይ ሰው በ10 የዱባይ ዲናር አንድ ምሳ ገዝቶ እያመጣ እንዲሰጥ አደረጉ። በዚህም ያ! 828 ሜትር የሚረዝመው ሰማይ ጠቀስ ፎቅ በፆመኞች ስንቅ ተሞላ። ከዘጠኝ ቀናት በፊት በተጀመረው የበጎነት ጥሪ መሠረትም እስከ ትናንት ድረስ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆን ምግብ መግዣ ገንዘብ ተሰበሰበ፡፡
ሞሮኮ ወርልድ ኒውስ ጋዜጣ ላይ ትናንት ማታ እንዳነበብኩት በዱባይ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በወረርሽኙ ታምመዋል።
ሥራ ፍለጋ የመጡትም የሚያሠራቸው ጠፍቶ ለበሽታው ተጋልጠዋል። የሰው አገር ሰዎቹም አንገት ማስገቢያና አንድ ጉርሻ አጥተዋል።
በየዚዳን ሐሰን
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡