ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ሽግግር ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መኾኗን በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ገለጹ።

26

ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ከተመድ ዲጂታልና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂስ አንደር ሴክሬታሪ ጀኔራል አማንዲፕ ሲንግ ጊል (ዶ.ር) ጋር ተወያይተዋል።

መድረኩ ዲጂታልና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂዎች አብዮታዊ አቅም በኢትዮጵያ እና በተቀረው ዓለም በአሥተዳደር፣ በኢኮኖሚ ልማት እና በማኅበረሰብ ግንባታ ላይ ያላቸውን አንድምታ ለመቃኘት ያለመ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ሽግግር ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መኾኗን ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፋዊ ደንቦችን በማውጣት ያለውን ወሳኝ ሚና በመረዳት ከትሩፋቶቹ ተጠቃሚ ለመኾን በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡:

ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት፣ በአሥተዳደር እና በሰው ኀይል ግንባታ ላይ በማተኮር የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገት የሚቀሰቅሱ ጠንካራ ፖሊሲዎችን እና ተቋማትን አቋቁማለች ብለዋል። ዓለም አቀፍ አጋርነትን በማሳደግ ያለውን ተጨባጭ ጥቅም ለማሳየት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቴክኖሎጂ ክፍሎች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዚህ ራዕይ ቁርጠኛ ነች ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በተመድ የሚኖሩ መልካም አጋጠሚዎችን ሁሉ አሟጣ ለመጠቀም ያላትን ዝግጁነት ተናግረዋል።

የተመድ ዲጂታልና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂስ አንደር ሴክሬታሪ ጀኔራል አማንዲፕ ሲንግ ጊል (ዶ.ር) ሃገራት በዲጂታል ዓለም እኩል ተጠቃሚ የሚኾኑባቸውን አማራጮች እና የአሥተዳደር ማዕቀፎችን በማየት ይበልጡን ተሳታፊ መኾን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ከተጀመሩ በርካታ እድሎች ተጠቃሚ የሚኾኑበትን ማዕቀፍ እንዲጠቀሙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ለልማት ተነሽዎች የቤት መሥሪያ ቦታ ለማስተላለፍ የእጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት አካሄደ።
Next articleታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አዲስ እና ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ ኾኗል።